በህንድ በአንድ ቀን ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ 19 ተያዙ
በሀገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ14 ሚሊየን ወደ 15 ሚሊየን ለመድረስ 4 ቀናት ብቻ ነው የወሰደው
ህንድ እስካሁን 132 ሚሊየን 330 ሺህ 644 ዜጎቿን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ከትባለች
ህንድ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ 19 መያዛቸውን አስታወቀች።
ይህም በዓለማችን ላይ በአንድ ቀን ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛ ኮቪድ 19 ተጠቂዎች ቁጥር መሆኑንም የሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘገባ ያመለክታል።
የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር በዛሬው እለት ባወጣው መረጃ በ24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ ምርመራ 314 ሺህ 835 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም በሀገሪቱ በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 15 ሚሊየን 930 ሺህ 965 የደረሰ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥርም 2 ሚሊየን 291 ሺህ 428 መድረሱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በሀገሪቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ 2 ሺህ 104 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በሀገሪቱ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 184 ሺህ 657 መድረሱንም ነው ሀገሪቱ ያስታወቀችው።
በህንድ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ14 ሚሊየን ወደ 15 ሚሊየን ለመድረስ አራት ቀናት ብቻ እንደወሰደበትም ተነግሯል።
በሀገሪቱ እያጋጠመ ያለው የሆስፒታል አልጋና የኦክስጅን እጥረት ሁኔታውን አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው እየተነገረ ይገኛል፡፡
በሀገሪቱ ቫይረሱን ለመከላከል የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባቶችን ለዜጎቿ እየሰጠች ሲሆን፤ እስካሁንም 132 ሚሊየን 330 ሺህ 644 ዜጎቿን መከተብ ችላለች።