ሩሲያ የወሰደችው እርምጃ አሜሪካ በዲፕሎማቶቿ ላይ ለወሰደችው ተግባር አጸፋ መሆኑን አስታውቃለች
ሩሲያ በሀገሯ የሚገኙ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን እያባረረች መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ አስታውቋል።
ዲፕሎማቶቹ ከሩሲያ የተባረሩት አሜሪካ ኒውዮርክ መቀመጫው ባደረገው የተመድ ዋና መስሪያ ቤት ይሰሩ የነበሩትን 12 ሩሲያውያን ዲፕሎማቶችን ላይ ለወሰደችው ተመሳሳይ እርምጃ አጸፋ መሆኑን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናትናው እለት በሩሲያ የአሜሪካ ዲፕሎማቲክ ኃላፊን በመጥራት ከሀገር ለቀው እንዲወጡ የታዘዙ የዲፕሎማቶችን ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ እንደሰጣቸው አስታቋል።
ሆኖም ግን ምን ያክል የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ሩሲያን ለቀው እንደሚወጡ በቁጥር የተገለፀ ነገር የለም።
ከሳምንታት በፊትም አሜሪካ ኒውዮርክ መቀመጫው ባደረገው የተመድ ዋና መስሪያ ቤት ይሰሩ የነበሩትን 12 ሩሲያውያን ዲፕሎማቶችን ማባረሯ ይታወሳል።
አሜሪካ ዲፕሎማቶቹን "ለሀገራዊ ደህንነታችን ጠንቅ የሆኑ የስለላ ስራዎችን ሲሰሩ የነበሩ የመረጃ ሰዎች" ናው በሚል እንዳባረረች መግለጿም ይታወሳል።
በተመሳሳይ ሩሲያ ከዚህ ቀደም በሞስኮ የአሜሪካ ኤምባሲ የሚሽኑ ምክትል ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የነበሩትን ባርት ጎርማንን ማባረሯ ይታወሳል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ቃል አቀባይ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፤ "ሩሲያ በእኛ ዲፕሎማት ላይ የወሰደችው እርምጃ ነገሮች የሚያባብስ ነው፤ እኛም ምላሻችንን እያጤንን ነው" ብለዋል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ሶስት ዓመት እና ከዚያ በላይ በአሜሪካ የሚኖሩ የሩሲያ ዲፕሎማቶች እስከ ቀጣዩ ጥር ወር ድረስ አገሯን ለቀው እንዲወጡ ማዘዘዟ አይዘነጋም።
በአሜሪካ ውሳኔ የተበሳጨች የምትመስለው ሩሲያ በወቅቱ ተመሳሳይ ውሳኔ ማስተላለፏን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ገልጻ ነበር።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በወቅቱ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ሶስት ዓመት እና ከዚያ በላይ በሩሲያ የሚኖሩ አሜሪካዊ ዲፕሎማቶች እስከ ጥር 2022 ዓመት ድረስ ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን ገልጸዋል።
ይህ እንዲሆን የፈለገችው አሜሪካ ናት ያሉት ቃል አቀባይዋ ሩሲያም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች ሲሉ አክለዋል።