9 ቢሊየን ለመድረስም 15 አመታት ያስፈልጓታል ተብሏል
የአለም ህዝብ ቁጥር ዛሬ 8 ቢሊየን መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት ይፋ አድርጓል።
ምድራችን ከ12 አመት በፊት ነበር 7 ቢሊየን የሰው ልጆች መኖሪያ መሆኗ የተገለፀው።
"8 ቢሊየን መድረሳችን ስናበስር ብዝሃነት እና እድገታችን ልናከብር ይገባል፤ ሁላችንም የሰው ልጆች ለምድራችን ሃላፊነትን መጋራት አለብን" ብለዋል የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ።
የተመድ ትንበያ እንደሚያሳየው፥ የአለም ህዝብ ቁጥር በ2030 8 ነጥብ 5 ቢሊየን፣ በ2050 9 ነጥብ 7 ቢሊየን፣ በ22ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ በ2100 ደግሞ 10 ነጥብ 4 ቢሊየን ይደርሳል።
ቀጣይ 1 ቢሊየን ህዝብ ለማግኘት 15 አመታትን መጠበቅ ያስፈልጋል ተብሏል( በፈረንጆቹ 2037 9 ቢሊየን እንደርሳለን)
ይህም የእድገት ምጣኔው እየቀነሰ መሄዱ እንደማይቀር ያመላክታል።
ከአለማችን አህጉራት እስያ በርካታ ህዝብ የሚኖርባት ሆና ቀጥላለች።
ምስራቅና የደቡብ ምስራቅ እስያ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ህዝብ ይኖርበታል፤ ይህም የምድራችንን 29 በመቶ የህዝብ ቁጥር ይይዛል። የመካከለኛው እና ደቡባዊ እስያም 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ሰዎች መኖሪያ መሆኑ ነው የተነገረው።
ቻይና እና ህንድ ብቻ በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ከፕላኔታችን የህዝብ ቁጥር 17 ከመቶውን ይዘዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ትንበያ እንደሚያሳየው ህንድ በቀጣዩ የፈረንጆቹ አመት ቻይናን በመብለጥ በህዝብ ቁጥር ቀዳሚውን ደረጃ ትይዛለች ተብሎ ይጠበቃል።
ምድራችን እስከ ፈረንጆቹ 2050 ከምታስመዘግበው የህዝብ ብዛት ግማሹ ከስምንት ሃገራት የሚመነጭ መሆኑም ተመላክቷል።
ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ፣ ፊሊፒንስ እና ታንዛኒያ ናቸው ፈጣን እድገት ያስመዘግባሉ የተባሉት።
የህዝብ ቁጥር እድገቱ ከአማካይ በህይወት የመቆያ እድሜ መጨመር ጋር የተያያዘ ነው።
በ2019 የአለም አቀፍ አማካይ በህይወት የመቆያ እድሜ 72 ነጥብ 8 አመት መድረሱ ይታወሳል፤ ይህም በ1990 ከነበረበት በ9 አመት እድገት ያሳየ ነው።
የሞት ምጣኔው እየቀነሰ በ2050 አማካይ በህይወት የመቆያ እድሜ (በአለም አቀፍ ደረጃ) ወደ 77 ነጥብ 2 አመት ከፍ እንደሚል የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል።
አለም አቀፋዊ አማካይ እድሜው ለሴቶች 73 ነጥብ 8 አመት ለወንዶች ደግሞ 68 ነጥብ 4 አመት ነው።
የመውለድ ምጣኔው ግን እየቀነሰ ነው። በ1950 ሴቶች በአማካይ 5 ልጆችን ይወልዱ ነበር። በ2019 ግን አማካዩ ወደ 2 ነጥብ 3 ልጆች ዝቅ ብሏል። ይሄው አማካይ በ2050 ወደ 2 ነጥብ 1 እንደሚወርድ ነው የተገመተው።
የውልደት ምጣኔው እየቀነሰ ቢሄድም በህይወት የሚቆዩት እየላቁ ይሄዳሉና ከ15 አመት በኋላ 9 ቢሊየን እንደርሳለን ብሏል የመንግስታቱ ድርጅት።