በሩሲያ ክሬምሊን ቤተ መንግስት አካባቢ ጥጃዋን ይዛ ለተቃውሞ የወጣችው አሜሪካዊት ታሰረች
የእንሰሳት መብት ተሟጋቿ አሊሻ ዴይ፥ “ጥጃዬን ከተማ ላሳየውና ሊበላ እንደማይገባ ተቃውሞዬን ላሰማ ይዤው ወጥቻለሁ” ብላለች
ዴይ ከአመታት በፊትም በቤቷ ውስጥ የምታኖረውን አሳማ ምግብ ቤት ይዛ በመሄድ መነጋጋሪያ መሆኗ ይታወሳል
በሩሲያ መዲና ሞስኮ የሚገኘው ታሪካዊው ቀዩ አደባባይ ከትናንት በስቲያ የተለየ ክስተት አስተናግዷል።
አሜሪካዊቷ የእንሰሳት መብት ተሟጋች አሊሻ ዴይ ከጥጃዋ ጋር ሰበር ሰካ ብላበታለች።
“ዶክተር ካው” የሚል ስም የሰጠችውን ጥጃ “ከተማ ላሳየውና በዚያውም ለመብቱ ልቆረቆርለት ስለፈለኩ አብረን ወጥተናል” ነው ያለችው ዴይ ከሩሲያው ታስ የዜና ወኪል ጋር ባደረገችው ቆይታ።
የእንሰሳት ተዋጽኦዎችን የማትመገበው ዴይ፥ “እንሰሳት ምግብ አይደሉም” በሚል ድምጿን ከፍ አድርጋ ማሰማቷን ተከትሎም በቁጥጥር ስር ውላለች።
በሞስኮ የትሬቨስኪ አካባቢ ፍርድ ቤትም ያለህጋዊ ፈቃድ በአደባባይ ተቃውሞን በማሰማት ወንጀል 20 ሺህ የሩሲያ ሩብል ወይም 261 ዩሮ እንድትከፍል ወስኖባታል።
“በድርጊቴ አልጸጸትም” ያለችው ዴይ ባለፈው ወር ወደ ሩሲያ በቱሪስት ቪዛ መግባቷን የታስ ዘገባ አመላክቷል።
በእንሰሳት ደህንነት ላይ በሚሰራ ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ የምትሰራው አሜሪካዊት የመብት ተሟጋች፥ ሰባት የአሳማ እና ሶስት የላም ጥጃዎችን እየተንከባከበች ነበር ተብሏል።
አትክልት ብቻ ተመጋቢዋ አሊሻ ዴይ በ2019ኝም በእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ እንደነበረች ዘ ሰን አስታውሷል።
እንስቷ በለንደን በሚገኝ መኖሪያ ቤቷ የምታኖረውን የአሳማ ጥጃ “ጂሲ ፒክሲ” የሚል ስም አውጥታለት ወደ ምግብ ቤቶች ይዛው መሄድና በታክሲም አብሯት እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የአንድ ሰሞን የጋዜጦች ርዕስ ሆና ነበር።
ይህ ድርጊቷ ከእንሰሳት ተፈጥሯዊ አኗኗር ጋር አብሮ የማይሄድ ነው በሚልም በቤቷ የተለየ ክፍል ያዘጋጀችለትን አሳማ ወደቀደመ መኖሪያው እንድትመልስ ተደርጓል።
አሊሻ ዴይ ወደ ምስራቅ አውሮፓ በማምራትም በፖላንድ እና ዩክሬን ተመሳሳይ የእንሰሳት መብት ተቆርቋሪነቷን ያሳያሉ ብላ ያመነችባቸውን ስራዎች መስራቷንም ዘ ሰን አውስቷል።
ይህ ብዙም ያልተለመደው “እንሰሳት መታረድ የለባቸውም” የሚል የተቃውሞ እንቅስቃሴዋ ግን ከለንደን እስከ ሞስኮ ከእስር እና ቅጣት ውጭ ያመጣላት ለውጥ ያለ አይመስልም።