ፖለቲካ
የህንዱ የጦር አዛዥ ጄነራል ቢፒን ራዋት በሄሊኮፕተር መከስከስ አደጋ ህይወታቸው አለፈ
ጄነራል ቢፒን ራዋት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራሞዲ የቅርብ ሰው ናቸው ተብሏል
አዛዡ ወደ መከላከያ አገልግሎት ስታፍ ኮሌጅ በማምራት ላይ ሳሉ አደጋው መከሰቱ ተገልጿል
የህንዱ ጦር አዛዥ ጄነራል ቢፒን ራዋት ተሳፍረውባት የነበረችው ወታደራዊ ሄሊኮፕተር በመከስከሷ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ዛሬ ጠዋት የሕንድ መከላከያ ኃላፊ ጄነራል ቢፒን ራዋትን የያዘ ሄሊኮፍተር መከስከሷን የሀገሪቱ አየር ኃይል አስታውቆ ነበር፡፡
የ63 ዓመቱ የመከላከያ ኃላፊ ሩሲያ ሰራሽ በሆነችው ኤምአይ 17ቪ5 ሄሊኮፍተር ሲጓዙ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አደጋው የተከሰተው በደቡብ ሕንድ በምትገኘው ታሚል ናዱ መሆኑንም አየር ኃይሉ አስታውቋል ተብሏል፡፡
ጄነራል ቢፒን ራዋት የመከላከያ ስታፍ ኃላፊ በመሆን የመጀመሪያ ሲሆን በዚህ ኃላፊነት የተሾሙም የመጀመሪያው የጦር መሪ ናቸው፡፡ ጄነራሉ፤ባለቤታቸው እና ሌሎች 11 ሰዎች በበረራ ላይ የነበሩ ሲሆን ሁሉም ህይወታቸው አልፏል ተብሏል፡፡
ጄነራል ቢፒን ራዋት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራሞዲ የቅርብ ሰው መሆናቸውም ይገለጻል፡፡ በዚህ አደጋ እስካሁን የደረሰው ጉዳት እየተጣራ መሆኑን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡