‘ኤር ኢንዲያ’ የተሸጠው ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉን ተከትሎ ነው
ከፍተኛ የብድር ጫና ያለባት ህንድ ብሔራዊ ምልክቷ የሆነውን ‘ኤር ኢንዲያ’ን ሸጠች፡፡
ህንድ በኪሳራ ውስጥ የነበረውን ‘ኤር ኢንዲያ’ን የሸጠችው አውጥታ በነበረው የሽያጭ ጨረታ ነው፡፡
አየር መንገዱን ወደ ግል ባለሃብቶች ለማዛወር ህንድ ተደጋሚ ጨረታዎችን አውጥታ ነበር፡፡
ሆኖም ባለበት ከፍተኛ የእዳ ጫና ምክንያት ደፍሮ አየር መንገዱን ሊገዛ የሚችል አካል አልተገኘም ነበረ፡፡
አሁን ግን ‘ታታ ግሩፕ’ በቅርቡ የወጣውን ጨረታ አሸንፎ አየር መንገዱን መልሶ በእጁ አስገብቶታል ተብሏል፡፡
ግዙፉ የህንድ የተሽከርካሪ እና ብረት አምራች ኩባንያ ‘ታታ ግሩፕ’ በ180 ቢሊዮን ሩፒ (በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር) ነው ‘ኤር ኢንዲያ’ን ጠቅሎ የራሱ ያደረገው፡፡
አየር መንገዱ ‘ታታ ኤር ላይንስ’ በሚል እ.ኤ.አ በ1932 ነበር በታታ ኩባንያ የተመሰረተው፡፡ ሆኖም ከ20 ዓመት በኋላ መንግስት ጠቅሎት በብሔራዊ አየር መንገድነት ሲገለገልበት ነበር፡፡
በተመድ ስብሰባ ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን ተቃወሙ- አምባሳደር ዲና
ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪ አዲስ አለመሆኑ የሚነገርለት ‘ታታ ግሩፕ’ 8 ቢሊዮን ዶላር ከሚጠጋው የአየር መንገዱ እዳ 2 ቢሊዮን ያህሉን ይሸፍናል ተብሏል፡፡
‘ኤር ኢንዲያ’ የ‘ኢንዲያን ኤር ላይንስ’ አካል እንዲሆን ከተደረገበት ከ2007 ጀምሮ ትርፋማ አልነበረም፡፡ 8 ሺ ለሚጠጉ ሰራተኞቹ የሚከፍለውን ደሞዝ ጨምሮ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርጎ ነበር፡፡
ሰራተኞቹን ቢያንስ ለአንድ ዓመት ይዞ ለመቆየት የተስማማው ‘ታታ ግሩፕ’ የ120 አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነውን አየር መንገድ ከኪሳራ አላቆ ወደ ትርፋማነት ሊያሸጋግረው እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ጨረታውን ማሸነፋቸውን በታሪካዊነት የገለጹት የ‘ታታ ግሩፕ’ ሊቀመንበር ናታርጃን ቻንድራሴከረን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አየር መንገድ እናደርገዋለን ብለዋል፡፡
የህንድ የኮሮና ቀውስ የአፍሪካን የክትባት አቅርቦት ጎድቷል
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ አስተዳደር የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን ወደ ግል በማዛወር በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡
ገንዘቡ በኮሮና ወረርሽኝ የተጎዳው የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት እንዲያገግም ለማድረግ እና ሰፊ የስራ እድልን ለመፍጠር የሚውል ነው እንደ ‘ዘ ናሽናል’ ዘገባ፡፡