መንገዱን የሰራው ተቋራጭ የጀርመን ቴክኖሎጂ ተጠቅሜያለሁ ሲል ተሳልቋል
በህንድ ማሃራሽትራ ግዛት ጃልና የተሰኘው ወረዳ ነዋሪዎች ለአመታት የመንገድ ይገንባልን ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ አግኝቷል።
የ”አስፋልት” መንገዱም ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የአመታት ጥያቄያቸው መመለሱ ያስደሰታቸው የካርጃት ሃስት ፖክሃሪ መንደር ነዋሪዎች ግን ደስታቸውን የቅጽበት ሆኖ እንዲቀር የሚያደርግ ክስተት ገጥሟቸዋል።
የጠጠር መንገዳቸው የለበሰው አስፋልት በቀላሉ እንደምንጣፍ ሊነሳ የሚችል በሌላ ቋንቋም ጥቁር ምንጣፍ ሆኖ አግኝተውታል።
በእጃቸው ሲያነሱትም ከስሩ ጨርቅ ነገር ለብሶ ከላዩ ላይ በስሱ አሽዋና ሬንጂ ተደርጎበት የተሰራ መሆኑንም ያረጋግጣሉ።
ነዋሪዎቹ አስፋልቱን በእጃቸው ሲያነሱት የሚያሳይ ምስል ተለቆም ህንዳውያንን ሲያነጋግር መሰንበቱን ነው ዘ ኢኮኖሚክ ታይምስ ያስነበበው።
በምስሉ ላይ ነዋሪዎች የአስፋልት ስያሜን ብቻ የያዘውን መንገድ የገነባውን ተቋራጭ ሲወቅሱና ለህግ ይቅረብልን ብለው ሲጠይቁ ይደመጣል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የገጠር መንገድ ፕሮግራም የተሰራው መንገድ ምን ያህል ከደረጃ በታች መሆኑን ያጋለጠ ሲሆን፥ በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ድርጊት እንዳይቀጥል ማንቂያ ሆኗል ተብሏል።
መንገዱን የገነባው ተቋራጭ ግን አዲስ የጀርመን ቴክኖሎጂ መጠቀሙን በመግለጽ መሳለቁ ተነግሯል።
በህንድ ባለፈው ሳምንትም ግንባታ ላይ የነበረ ግዙፍ ድልድይ ሳይጠናቀቅ በአመት ለሁለተኛ ጊዜ መፍረሱ የሚታወስ ነው።
በጋንጋ ወንዝ ላይ እየተገነባ የነበረው ድልድይ ሃጋሪያ እና ባጋልፑር የተሰኙትን ወረዳዎች እንዲያገናኝ ነበር ከአመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው።
በ2020 ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ድልድይ ለሁለተኛ ጊዜ ፈርሶ ወደ ወንዝ ሲገባ መንገደኞች በስልካቸው ቀርጸውታል።
በምስራቃዊ ህንድ ቢሃር የደረሰው የድልድይ መደርመስ አደጋ የግንባታ ጥራት ጉድለት ማሳያ ተደርጎ እየተነሳ ነው።