ከፈጣሪ ልዩ ጥበቃ እንደሚደረግለት ለማሳየት አንበሳ በእጆቹ የዳበሰው ፓስተር
በመጽሃፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው ዳንኤል ከአንበሳ መንጋጋ የማምለጥ ልዩ ጸጋ አለኝ ያለው “ፓስተር ዳንኤል” አማኞችን ይህን “ተአምር” እንዲመለከቱ ጋብዟል
ከ30 አመታት በፊት መሰል ሙከራ ያደረገ ናይጀሪያዊ ፓስተር በአንበሳ ተበልቶ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል
ከፈጣሪ የተላከ እና ልዩ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን ለአማኞች ማሳየት የፈለገው ናይጀሪያዊ ፓስተር ወደ አንበሳ ግቢ በማምራት “ጸጋዬን እዩልኝ” ብሏል።
ኪንግ ቱንዴ ኢድኑት የተባለ ግለሰብ በኢንስታግራም ገጹ በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ሰማያዊ ሱፍ የለበሰው ፓስተር በብረት አጥር በተዘጋ የአናብስት መኖሪያ ውስጥ ይታያል።
ፓስተር ዳንኤል የሚል ስም እንዳለው የተጠቀሰው ግለሰብ በሶስት አናብስት መሃል ሆኖ እየደባበሳቸው ለማዝናናት ሲሞክር ያሳያል ቪዲዮው።
“ተአምራቱን” እንዲመለከቱ የጋበዛቸው አማኞችም ከብረት አጥሩ ውጭ በስጋት ውስጥ ሆነው ሁኔታውን በስልካቸው ሲቀርጹት ይታያል።
ፓስተር ዳንኤል ወደ አንበሳ ግቢ በድፍረት የገባው የተለየ የፈጣሪ ጸጋ እንዳለውና ምንም ሃይል (አንበሳም ቢሆን) እንደማይነካው ለማሳየት በማለም ነው።
አንደኛው ደቦል የፓስተሩን እጅ ወደ አፉ ለማስገባት ሲሞክር ቀርጥፎ ይበላው ይሆን የሚል ስጋትን ያጭር ነበር።
በፈረንጆቹ 1991 “ነብይ ዳንኤል አቦዱሪን” የተባለ ናይጀሪያዊ እንደ መጽሃፍ ቅዱሱ ዳንኤል ከአንበሳ መንጋጋ መውጣት የሚያስችል ሃይል አለኝ ብሎ ዘው ባለበት የኢባዳን ዩኒቨርሲቲ አንበሳ ማቆያ በአናብስት ተቀረጣጥፎ የመበላቱን ዜና ሶስት አስርት ቢያልፈውም ማውሳቱ ተገቢ ስለመሆኑም በማከል።
ባለሰማያዊ ሱፉ ፓስተርም ስሙ ዳንኤል መሆኑና የተለየ መንፈሳዊ አቅም እንዳለው ለማሳየት አማኞችን ወደ አንበሳ ግቢ ይዞ ማምራቱ ከ”ነብይ ዳንኤል አቦዱሪን” ጋር ቢያመሳስለውም በህይወት ተርፏል።
በኢንስታግራም ከተለቀቀው የቪዲዮ ምስል ስር በርካቶች አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሲሆን፥ ከ30 አመት በፊት ነፍስ የቀጠፈውን አደገኛ ሙከራ የደገመው ፓስተር ትችቱ በርትቶበታል።