የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ በዩክሬን ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
ጠቅላይ ሚንስትሩ በሩስያ እና ዩክሬን መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ለመጀመርያ ጊዜ ነው በወደ ኬቭ የሚያቀኑት
ህንድ እና ሩስያ በጂኦፖለቲካዊ ግንኙነት እና በንግድ ጠንካራ ትስስር ያላቸው ሀገራት ናቸው
የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ በመነሀሴ መጨረሻ ወደ ዩክሬንን እንደሚጎበኙ ተነገረ፡፡
ለሶስተኛ ጊዜ የስልጣን ዘመን ቃለ መሀላ ከፈጸሙ በኋላ በመጀመርያ ይፋዊ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸው በቅርቡ ሩሲያ የነበሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ በዩክሬን እና በሩስያ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኬቭ ያቀናሉ።
ሞዲ ፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ ባዘጋጁት የተለያዩ የሰላም ጉባኤዎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቢቀርብላቸውም ሳይታደሙ ቀርተዋል፡፡
ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ያላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ሩስያ ላይ ጫና ለማሳደር እና እና ማዕቀብ ለመጣል በተደረጉ የተመድ እና የሌሎች የባለ ብዙ ወገን ጉባኤዎች ላይ ገለልተኛ ሆነው ዘልቀዋል።
አሜሪካ እና ምእራባውያን በጦርነቱ ምክንያት ሩስያ ካለም አቀፉ ማህበረሰብ እንድትገለል እንዲሁም በኢኮኖሚያዋም ላይ ጫና ለመፍጠር ላሰቡት እቅድ ህንድ እና ቻይና እንቅፋት የሆኑ ይመስላል፡፡
የተለያዩ የአውሮፓ ግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት መሪዎች ከአንድም ሁለት ጊዜ በዩክሬን ተገኝተው አጋርነታቸውን ሲገልጹ ሞዲ ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ እንድም ጊዜ ወደ ስፍራው አላቀኑም፡፡
በቅርቡ በሩስያ የነበራቸውን ጉብኝት ተከትሎ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በኤክስ ገጻቸው የአለም ትልቁ ዴሞክራሲ ከአለም ትልቁ ወንጀለኛ ጋር ሲተቃቀፍ ማየት ያሳፍራል የሚል ጽሁፍ አስፍረው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም በህንድ የሚገኙት የዩክሬን አምባሳደር በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በህንድ መንግስት ታዘው ነበር፡፡
በሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉት ምእራባውያን ሁለቱን ሀገራት ከማቀራረብ እና ከማደራደር ይልቅ ለዩክሬን ይፋዊ ውግንናቸውን ገልጸው ጦርነቱን መደገፍ መርጠዋል በዚህ መካከል ጦርነቱ ሶስት አመቱን ሊደፍን ጥቂት ጊዜያት ቀርተውታል፡፡
የተለያዩ የአለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት ተመራማሪዎች የዩክሬን ግጭት ወደ እጅ አዙር ጦርነት ከተቀየረ መሰነባበቱን ያነሳሉ፡፡
ይህን ጦርነት ለመቋጨት የአሜሪካ እና ምእራባውያን የጦር መሳርያ ድጋፍ እንዲሁም ተጽእኖ የሰራ አይመስልም በመሆኑም ግጭቱ ይቆም ዘንድ ወይ እንደ ህንድ እና ቻይና ያሉ በሩስያው ፕሬዝዳንት ላይ በጎ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ አካላት ወደ ፊት መምጣት ይኖርባቸዋል ካልሆነም ደግሞ አንዱ ሀገር እስኪሸነፍ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ቪክተር ኦርባን ሁለቱን ሀገራ ለማቀራርብ አድርገውት የነበረው የዲፕሎማሲ ጉዞም ከአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ሲኤንኤን ላይ ትንታኔ የሚጽፈው ሳይመን ማካርቲ ምእራቡ የተሳነውን አልያም ችላ ያለውን የማሸማገል ስራ ቻይና ተሳክቶላታል ሲል ጽፏል፡፡
በዚህ ሳምንት የፍልስጤም ተቀናቃኞቹን ፋታህ እና ሃማስ አብረው እንዲሰሩ እና ከግጭት እንዲወጡ ያስማማችው ቤጂንግ ከዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚተሮ ኮሊባ ጋር ተወያይታለች፡፡
በቻይና ከፍተኛ የዩክሬን በለስልጣን ከጦርነቱ በኋላ ጉብኝት ሲያደርግ ይህም ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
ቤጂንግ እና ደልሂ ሩስያ እና ዩክሬንን ለማደራደር አብረው ቢሰሩ ሁነኛ ውጤት ላይ ሊደርሱ እንደሚችል ይገመታል ለዚህም የአሁኑ የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ዩክሬን የሚያደርጉት ጉብኝት ወሳኝነቱ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡