የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ ወደ ሞስኮ ሊያቀኑ ነው
ጠቅላይ ሚንስትሩ በሞስኮ በሚኖራቸው ቆይታ በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል
በዩክሬን ጦርነት አለምአቀፋዊ መገለል የደረሰባት ሩሲያ ወሳኝ አጋር ከሆኑ ጥቂት ሀገራት መካከል ህንድ አንዷ ናት
የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ሞስኮ እንደሚያቀኑ ተነገረ፡፡
በቅርቡ በህንድ በተደረገ አጠቃላይ ምርጫ ለ3ተኛ ግዜ የስልጣን ዘመን ያሸነፉት የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ በአዲሱ የስልጣን ዘመናቸው በሚያደርጉት የውጭ ሀገራት የመጀመሪያ ጉብኝት በጦርነት እና በአለምአቀፋዊ ተጽእኖ ውስጥ የምትገኝውን ሩሲያን መርጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሞስኮ የሚመጡበትን ቀን ይፋ ያላደረገው ክሪሚሊን ሞዲ በሞስኮ በሚኖራቸው ቆይታ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በቀጠናዊ እና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ አስታውቋል፡፡
ሩሲያ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ጫና ውስጥ በምትገኝበት ወቅት ሞዲ የሚያደርጉት ጉብኝት ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ ከምእራባዊያን ወደ ሞስኮ የተወነጨፈውን የማዕቀብ ማዕበል ፑቲን ከተቋቋሙባቸው መንገዶች መካከል ከህንድ ጋር ያለቸው ከፍተኛ ንግድ ግንኙነት ይጠቀሳል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በዲንጋይ ከሰል እና በነዳጅ ምርቶች ላይ ያላቸው ግብይት መጨመሩ ሲገለጽ የምዕራባዊያንን ማእቀብ ተከትሎ ሀገራቱ በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት የደረሱት ውሳኔም ወሳኝ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
በ2023 በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው የንግድ ግንኙነት 65 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነው፤ የንግድ ልውውጡ 50 ቢሊዮን ዶላርን ሲሻገርም ይህ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
በዚሁ አመት ህንድ ከሞስኮ የምታስገባቸው ምርቶች መጠን በ 1.8 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ደልሂ ወደ ሩሲያ የምትልካቸው ምርቶች ደግሞ በ1.4 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ይህም ሩሲያን የህንድ 4ተኛ ግዙፍ የንግድ አጋር እንድትሆን ያስቻላት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በነዳጅ እና በተለያዩ ምርቶቿ ላይ እንዲሁም በአጠቃላይ የፋይናንስ እንቅስቀሴዎቿ ላይ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ ከፍተኛ ጫና የተጣለባት ሞስኮ ከህንድ እና ከቻይና ጋር የምታደርገው ግብይት ለኢኮኖሚያዋ ሳይዳከም መቀጠል ወሳኝ ነው፡፡
ከንግድ ግንኙነት ባለፈ በተለያዩ አለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚቆሙት ሀገራት በብሪክስ ስብሰብ ውስጥ ያላቸው ግንኙነት ወዳጅነታቸው እንዲጠነክር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡
በቅርቡ ዩክሬን በሲውዘርላንድ ባዘጋጀችው የሰላም ጉባኤ ላይ የህንድ አለመሳተፍ በተዘዋዋሪ አጋርነቷን ለሞስኮ የገለጸችበት መንገድ ሆኖ ተወስዷል፡፡