ረጅም ስአት መተኛት ብቻ ለሽልማት እንደሚያበቃ ያውቃሉ?
በህንድ ለሶስተኛ ጊዜ በተካሄደ ውድድር “የእንቅልፍ ሻምፒዮን” የሆነችው ወጣት 10 ሺህ ዶላር ተሸልማለች
ውድድሩን ያዘጋጀው ተቋም ባለፉት ሶስት አመታት ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለመሳተፍ አመልክተዋል ብሏል
በህንድ ብዙዎች አጥተውታል የተባለው እንቅልፍ በውድድር መልክ መጥቷል።
የቤንጋሉሩ ከተማ ወጣቷ ሳይሽዋሪ ፓቲልም “የእንቅልፍ ሻምፒዮን” ሆና የ900 ሺህ የህንድ ሩፒ ወይም 10 ሺህ 736 ዶላር ሽልማት አሸናፊ ሆናለች።
“ዌክፊት” የተባለ ተቋም እንቅልፍን የሚያበረታታ ተቋም ሶስተኛውን ውድድር ከሰሞኑ አካሂዷል።
ተቋሙ አመልካቾችን አወዳድሮ በውድድሩ የሚሳተፉና ስልጠና የሚወስዱ ሰዎችን ይመርጣል።
ለዘንድሮው ውድድርም 12 ለእንቅልፍ ትልቅ ዋጋ የሚሰጡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ቅድሚያ ያልሰጡ 12 አመልካቾች ተመርጠው ስልጠና እየወሰዱ እግረመንገድ ሽልማት የሚያስገኝ ውድድር ላይ ተሳትፈዋል ነው የተባለው።
እያንዳንዱ ተወዳዳሪ እጅግ ምቹ ፍራሽ የተሰጣቸው ሲሆን ሰላማዊና ጥራት ያለው እንቅልፍ መተኛታቸውን የሚከታተሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችም ተወዳዳሪዎቹን በአንክሮ ሲከታተሉ ነበር ብሏል ዘ ሂንዱ በዘገባው።
ተወዳዳሪዎቹ በቀን ከስምንት እስከ ዘጠኝ ስአት እንዲሁም የ20 ደቂቃ አነቃቂ ሸለብታ (ናፕ) እንዲያደርጉ በእንቅልፍ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷቸው ነው “የእንቅልፍ ሻምፒዮን” ክብርን ለመቀዳጀት የተፋለሙት።
ውድድሩን ያዘጋጀው ተቋም ባለፉት ሶስት አመታት ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለመሳተፍ አመልክተዋል፤ ለተወዳዳሪዎች ከ75 ሺህ ዶላር በላይ ክፍያ ተፈጽሟል ብሏል።
ከህንድ ዜጎች ውስጥ ግማሹ ከእንቅልፉ ሲነሳ ድካም ይሰማዋል የሚለው አወዳዳሪው “ዌክፊት”፥ ይህም ለረጅም ስአት ከመስራት፣ ጭንቀትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ እንደሚመነጭ ያብራራል።
ውድድሩና ስልጠናውም ጤናማ እንቅልፍን ለማበረታታት እያገዘ እንደሚገኝ ነው የኩባንያው የማርኬቲንግ ሃላፊ ኩናል ዱቤይ የሚገልጹት።
የዘንድሮው “የእንቅልፍ ሻምፒዮኗ” የኢንቨስትመንት ባንክ ሰራተኛ ሳይሽዋሪ ፓቲል “በውድድሩ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ የምትተኛበት እና የምትነቃበት ጊዜ ወጥ መሆን አለበት፤ በጊዜ ለመተኛት ከስልክህና ከማህበራዊ ሚዲያዎች መራቅ ቢከብድም ልምምዱ ትልቅ ዋጋ ነበረው” ትላለች።
በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ረጅምና ጤናማ እንቅልፍ ለመተኛት መሞከር በራሱ አስጨናቂ መሆኑን ባትክድም “በውድድሩ የመጨረሻ እለት መረጋጋቴ አሸናፊ አድርጎኛል” ስትልም ለዘ ሂንዱ ተናግራለች።
አስገራሚው ውድድር እንቅልፍ ሰውነትን እንዴት እንደሚያድስና በሽታን የመከላከል አቅም እንደሚጨምር እንዲሁም ከአዕምሮ ቆሻሻን የማስወገድ ሃይሉን ያስተማራት እንደሆነ በመግለጽም አዘጋጆቹን አመስግናለች።