ለ30 አመታት እንቅልፍ ያልተኛችው ቬትናማዊት
በልጅነቷ ለንባብ ባላት ጥልቅ ፍቅር እራሷን ከእንቅልፍ ለማራቅ ያደረገቻቸው ሙከራዎች ለሶስት አስርተ አመታት አይኗን ሳትከድን እንድትዘልቅ አድርገዋታል
የህክምና ባለሙያዎች የግለሰቧን ሀሳብ ለማረጋገጥ ምርመራ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ናቸው
ቬትናማዊቷ የልብስ ስፌት ባለሙያ ከእንቅልፍ ጋር ከተፋታች 30 አመታት መቆጠራቸውን ተናግራለች፡፡
ኑጉየን ናጎክ የተባለችው የ49 አመት ቬትናማዊት ሎንግ አን የተባለ የቬትናም ከተማ ነዋሪ እንስት ለሶስት አስርተ አመታት አለመተኛቷ የበርካታ መገናኛ ብዙሀንን ቀልብ ስቧል፡፡
የአእምሮን በትክክል መስራት ከሚያረጋግጡ መሰረታዊያን መካከል አንዱ የሆነው እንቅልፍ ለአመታት ከእኔ ርቋል የምትለው ንጉየን እስካሁን በጤናዋ ላይ ያስከተለው ችግር አለመኖሩን ትናገራለች፡፡
ማንበብ በጣም እወዳለሁ የምትለው ግለሰቧ በልጅነቷ በምሽት ለረጅም ሰአት የማንበብ ልምድ እንደነበራት አንስታ ይህ ልምዷ እያደገ መጥቶ ላለፉት አስርተ አመታት እየተዳደረችበት የምትገኝው የልብስ ስፌት ሞያ ከእንቅልፍ ጋር ሙሉ ለሙሉ እንድትቆራረጥ ያደረጋት ምክንያት እንደሆነ ነው የተናገረችው፡፡
“የልብስ ስፌት ስራን ስጀምር በብዛት የሚመጡ ትዕዛዞችን በቀጠሮ ጊዜያቸው ለማድረስ አምሽቼ መስራት ጀምርኩ፤ ቀጥሎም ልጅ እያለሁ ምሽት ላይ ለማንበብ የማጠፋው የረጂም ጊዜ ልምድ አግዞኝ የእንቅልፍን አላስፈላጊነትን ሰውነቴ መለማመድ ጀመረ” ስትል ነው ከመገናኛ ብዙሀን ጋር በነበራት ቆይታ የገለጸችው፡፡
ስራውን በጀመረችባቸው የመጀመሪያ ወራት እንቅልፍ ያስቸገራት እና በስራም ላይ ትሳሳት እንደነበር ከዚህ ባለፈም መኪና እያሽከረከረች እንቅልፍ ወስዷት የትራፊክ አደጋ ጭምር ደርሶባት ያውቃል፡፡
ከእነዚህ አጋጣሚዎች በኋላ በልጅነቷ ታደርግ እንደነበረው ንቁ ለመሆን ውሳኔ ላይ የደረሰችው ንጉየን እንቅልፍ ላለመተኛት የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ጀመረች፡፡
“ሁሌም ከልብስ መስፊያ ማሽኔ ፊት ስቀመጥ ትዕዛዞችን ሳልጨርስ እንቅልፍ አይታሰብም በሚል ለራሴ እነግረዋለሁ፤ በኋላ ስራየን ከጨረስኩ በኋላ ለመተኛት ብፈልግ እንኳን መተኛት አልቻልኩም በዛው ሌሊቱን በስራ ማንጋት ቀጠልኩ፤ ሳምንታት ወራትን ወራት አመታትን አስከትለው 30 አመታትን አልተኛሁም ሰውነቴም የድካም ስሜት አይሰማውም” ነው ያለችው፡፡
የግለሰቧ የ30 አመት እንቅልፍ ማጣት ምክንያት እና እውነታነት እስካሁን በህክምና አልተረጋገጠም። ነገር ግን የአካባቢው ሰዎች እና ቤተሰቦቿ ግለሰቧ 24 ሰአት ሙሉ ያለ እንቅልፍ ልብስ ስትሰፋ እና ሌሎች ስራዎችን ስታከናውን እንደሚመለከቷት ተናግረዋል፡፡
የኑጉየን ታሪክ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀንን ትኩረት መሳቡን ተከትሎም የቬትናም የህክምና ባለሙያዎች በጤና ሁኔታዋ ላይ እና እንቅልፍ ሳተኛ ይህን ሁሉ አመታት እንዴት መዝለቅ እንደቻለች ምርመራ ሊያደርጉላት እየተዘጋጁ መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሀገሪቱ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ይህን ለማመን የሚከብድ አጋጣሚ ለማረጋገጥ ካሜራ ገጥመው የቀናት እንቅስቃሴዋን ለመቅረጽ ከግለሰቧ ፈቃድ ማግኝታችው ተነግሯል፡፡