ከጣራ ላይ በሚወድቅ አካል ላለመመታት ሲሉ ሄልሜት ለማድረግ የተገደዱት የመንግስት ሰራተኞች
የሚሰሩበት ተቋም ህንጻውን ማሳደስ ባለመቻሉ ሰራተኞቹ ሄልሜት ለማድረግ ተገደዋል
የሀገሪቱ መንግስት በቅርቡ ሰራተኞቹን ወደ ሌላ ህንጻ ለማዛወር ቃል ገብቷል
ከጣራ ላይ በሚወድቅ አካል ላለመመታት ሲሉ ሄልሜት ለማድረግ የተገደዱት የመንግስት ሰራተኞች
በህንዷ ቴላንጋና ግዛት ያለ አንድ መንግስታዊ የልማት ድርጅት ህንጻ ውሃ ማስገባቱን ተከትሎ ጣሪያው ተሰነጣጥቆ በስራ ላይ ባሉ ሰራተኞች ላይ እየወደቀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የድርጅቱ ሰራተኛ የሆነ አንድ ግለሰብ በቅርቡ ከጣሪያ ላይ በወደቀ አካል ጭንቅላቱን ተመትቶ ሆስፒታል ገብቷል ተብሏል፡፡
ይህን ተከትሎ ቀሪዎቹ ሰራተኞች የሞተር ሳይክል አደጋ መከላከያ ሄልሜት አድርገው ስራቸውን ለመቀጠል ተገደዋል፡፡
ሰራተኞቹ ለመንግስታቸው በተደጋጋሚ ህንጻው እያረጀ እና ውሃ እየገባበት በመሆኑ እንዲጠገን ቢያመለክቱም ሰሚ አልተገኘም ተብሏል፡፡
ስራቸውን ላለማጣት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚጠበቅባቸውን ለመስራት የተገደዱት እነዚህ ሰራተኞች የአደጋ መከላከያ ወይም ሄልሜት አድርገው ስራቸውን ሲቀጥሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለቀዋል፡፡
ህንድ የፍቅረኞች ቀን “ላሞችን በማቀፍ ቀን” እንዲተካ ያሳለፈችው ውሳኔ…
ሰራተኞቹ ላለፉት 12 ወራት በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ስራቸውን ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ ተንቀሳቃሽ ምስልም በበማህበራዊ ትስስር ገጾች በተጋራ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የበርካቶችን ትኩረት መሳቡ ሲገለጽ የሀገሪቱ መንግስትም ትችቶችን ማስተናገዱ ተገልጿል፡፡
ከህዝብ ቁጣ እና ትችት የበረታበት መንግስትም ሰራተኞቹን ወደ ሌላ ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ህንጻ እንደሚያዛውር አስታውቋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡