ህንዳውያን በፈረንጆቹ 2021 ከ75 ሚሊየን ዓመት ጋር የሚስተካከል ጊዜን በስልካቸው ላይ አሳልፈዋል
በዓመቱ በሀገሪቱ ከኢንተርኔት ዳወንሎድ የተደረጉ ይዘቶች ብዛትም 26 ነጥብ 6 ቢሊየን ነው ተብሏል
ህንዳውያን በስልካቸው ላይ ያሳለፉት አጠቃላይ ሰዓት 655 ቢሊየን ሰዓት ነው
አሁን አሁን በዓለማችን ላይ ስራችንን ለመስራትም ይሁን የሚያስፈልገንን ነገር እዛው ቤታችን ሆነን በእጅ ስልካችን ብቻ መከወን እና ማዘዝ የብዙዎች ልማድ እሆነ ከመጣ ዋል አደር ብሏል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ መከሰቱን ተከትሎ ደግሞ ሰዎች ስራቸውንም ይሁን ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎቶች የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ከቤታቸው ሆነው ለመከወን እንዲገደዱ ማድረጉ ይታወቃል።
‘አፕ አኔ’ የተባለው እና በኢንትርኔት ላይ ያሉ መረጃዎችን የሚሰበስብ ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ህንዳውያን በሞባይል ስልካቸው ላይ በሚያሳልፉት ሰዓት ብዛት ከዓለማችን ቀዳሚ እየሆኑ መጥተዋል ብሏል።
እንደ ‘አፕ አኔ’ መረጃ በፈረንጆቹ 2021 ብቻ እያንዳንዱ ህንዳዊ በሞባይል ስልኩ ላይ ያሳለፈው ጊዜ ሲደመር 655 ቢሊየን ሰዓት ደርሷል።
ህንዳውኑ በአጠቃላይ በሞባይል ስልካቸው ላይ ያሳለፉት 655 ቢሊየን ሰዓት ወደ ዓመት ሲቀየርም ከ75 ሚሊየን ዓመት ጋር እኩል መሆኑም ተነግሯል።
ህንዳውያን በፈረንጆቹ 2019 ዓመት 381 ቢሊየን ሰዓት በስልካቸው ላይ አሳልፈዋል የተባለ ሲሆን፤ ይህም ከ2021 ጋር ሲነጻጸር የ37 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
‘አፕ አኔ’ ባወጣው ልላ መረጃ በ2021 በሀገሪቱ ከኢንተርኔት የወረዱ (ዳወንሎድ) የተደረጉ መረጃዎች እና መገልገያዎች ብዛት 26 ነጥብ 6 ቢሊየን መሆኑን አስታውቋል።
ይህም በፈረንጆቹ 2019 ዓመት ጋር ሲነጻተር የ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ድርጅቱ ባወጣው መረጃው አመላክቷል።
በ2021 በህንድ ዳወንሎድ የተደረጉ ነገሮችን ስንመለከትም ጌም (መጫወቻዎች) በ9 ነጥብ 33 ቢሊየን ቀዳሚውን ሲይዝ፤ ከፋይናንስ ጋር የተያያዝ ዳወንሎዶች 1 ነጥብ 1 ቢሊየን፤ ከጤና ጋር የተያያዙ መረጃዎች ደግሞ በ50 ሚሊየን ዳወንሎድ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።