ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሀብትን የሚያስመልስ ዳይሬክቶሬት አደራጀ
ዐቃቤ ሕጉ በአገር ኢኮኖሚ እና ደህንነት ላይ የተለያዩ ወንጀሎችን የፈጸሙ አካላትን ለሕግ አቅርቦ በእስራት ማስቀጣት ብቻዉን በቂ አይደለም እንዳይደለ ገልጿል
ዳይሬክቶሬቱ ከጥር 01 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ ይገባል ተብሏል
በወንጀል ድርጊት የተገኘ እና በአገር ዉስጥ በተለያዬ መንገድ የተደበቀ ወይም ከአገር የሸሸ የሕዝብ ሃብትን ለማስመለስ የሚሰራ ዳይሬክቶሬት ማደራጀቱን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡
ዳይሬክቶሬቱ ከጥር 01 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገባም አስታውቋል፡፡
በአገር ኢኮኖሚና ደህንነት ላይ የተለያዩ ወንጀሎችን የፈጸሙ አካላትን ለሕግ አቅርቦ በእስራት ማስቀጣት ብቻዉን በቂ አይደለም ነው ያለው ዐቃቤ ሕጉ፡፡
እስራቱ አስተማሪ እንዳልሆነ የዓለም ተሞክሮም ሆነ የሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ያረጋገጠዉ ጉዳይ ነዉም ብሏል፡፡
ሌላ ወንጀልን ለመከላከልም ሆነ አጥፊዎች እንዲማሩበት ለማድረግ እንደማያስችልም ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም አጥፊዎችን በወንጀል ከመቅጣት ባሻገር በወንጀል ድርጊት ያገኙትን ሃብት ወደ ትክክለኛ ባለቤቱ (ሕዝብ እና መንግስት) እንዲመለስ ማድረግ አስፈላጊ ነዉና ጥቆማዎች እንዲሰጡት ጥሪ አቅርቧል፡፡
በርካታ ቁጥር ያለው ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ መሸሹ እና በተለያዩ ሃገራት እና ዓለም አቀፍ ባንኮች ጭምር መከማቸቱ ይነገራል፡፡
ይህን ገንዘብ ለማስመለስ በትኩረት እንደሚሰሩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመጀመሪያ የፓርላማ ንግግራቸውን ባደረጉበት ወቅት ጭምር አስታውቀው ነበር፡፡
የተባበሩ የተለያዩ ሃገራት ጭምር እንዳሉም ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የጠቀሱት፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠውን ትዕዛዝ በመከተል ቀደም ባሉት አመታት በእንዲህ ዓይነት መንገድ ከሃገር የሸሸውን ሃብት ለማስመለስ በመስራት ላይ መሆኑን አስታወቆ ነበር፡፡
ሆኖም እስካሁን ድረስ በስራው ያገኘው የሸሸ ወይም ያስመለሰው ሃብት እንዳለ ያስታወቀው ነገር የለም፡፡