ሁለቱ መሪዎች ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የተገናኙት በኦባማ አስተዳደር ወቅት ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ነው
ፕሬዝዳንት ባይደን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ዛሬ ተገናኝተው እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ውይይቱ በዋይት ሀውስ በሁለቱ ልዕለ ኃያላን ሀገራት መካከል የተካረረውን ግንኙነት መፍትሄ ያስቀምጣል የሚል ተስፋ ተሰንቋል።
ሁለቱ መሪዎች ከቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ቀደም ብሎ በባሊ ኢንዶኔዢያ ለመምከር ተስማምተዋል። ንግግሩ ሰዓት እንተቆረጠለት ያስታወቀው ዋይት ሀውስ ለሁለት ሰዓታት ይቆያል ተብሎ ይጠበቃልም ብሏል።
ዋይት ሀውስ በመሪዎቹ ምን እንደሚጠበቅ ከመናገር መቆጠቡን የዘገበው የአሜሪካው ኤንፒአር፤ ለዚህም ምክንያቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግልጽ አለመግባባት ነው ብሏል።
የባይደን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሌቫን ወደ ባሊ ለሚጓዙ ጋዜጠኞች እንደተናገሩት ባይደን ሙሉ በሙሉ ቀጥተኛ በሆነ መንግድ ፕሬዝዳንት ዢን ለመስማት እድሉ አለው ብለዋል።
ሱሌቫን እንዳሉት ዋይት ሀውስ መሪዎቹ ከዚያ ስብሰባ በተሻለ ግንዛቤ እና ይህንን ግንኙነት እና ፉክክርን በኃላፊነት ለመምራት የሚያስችል መንገድ ይዘው እንደሚወጡ ተስፋ አድርግዋል።
ከሆንግ ኮንግ እና ከታይዋን እስከ ደቡብ ቻይና ባህር ድረስ ባሉ በርካታ ጉዳዮች አሜሪካና ቻይና ከቅርብ አመታት ወዲህ ግንኙነታቸው ውጥረቱ ነግሶበታል። የኃያላኑ ሀገራት ግንኙነት በተለይም ባለፉት አስርት ዓመታት ወደ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ መውደቁ ይነገርታልም።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ባለፈው ነሐሴ ቤጂንግ ግዛቴ አካል በምትላት ታይዋን ካደረጉት ጉዞ በኋላ ውጥረቱ ጨምሯል። ጉብኝቱ ቻይናን ያስቆጣ ሲሆን በመቀጠልም አሜሪካ በታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ መጀመሯ ውጥረቱ እንዲያይል አድርጓል ነው የተባለው።
በኢንዶኖዥያው የባይደንና የጂንፒንግ ንግግድ ቀዳሚና ዋነኛ አጀንዳ ታይዋን እንደምትሆን ተነግሯል።
ከዚህ ባሻገርም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ሌላኛው የንግግር አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ተጠብቋል።
ባይደን በፈረንጆቹ ጥር 2021 ፕሬዝዳንት ከሆኑ ከፕሬዝዳንት ዥ ጋር አምስት የስልክ ወይም የቪዲዮ ውይይት አድርገዋል። ሁለቱ መሪዎች በመጨረሻ በአካል የተገናኙት በኦባማ አስተዳደር ወቅት ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ነው።