አሜሪካ ቲክቶክ የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችን እንደሚፈጥርባት ገለጸች
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ዳይሬክተር ቲክ ቶክ የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችን እንደሚፈጥር ተናግረዋል
ተወዳጅ መተግበሪያው ቤጂንግ መረጃ ለመሰብሰብና መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር ትጠቀምበታለች የሚል ስጋት ደቅኗል
በቻይና ባለቤትነት የተያዘው የቲክቶክ የአሜሪካ እንቅስቃሴው የብሔራዊ ደህንነት ስጋትን ያሳድጋል ሲሉ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስ ሬይ ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ የቻይና መንግስት የተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያ የሆነውን መተግበሪያ በተጠቃሚዎች ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ወይም መሳሪያዎቻቸውን ለመቆጣጠር ሊጠቀምበት የሚችል ስጋት እንዳለ አመልክተዋል።
ስጋቶች የቻይና መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ላይ መረጃ መሰብሰብ ወይም ስልተ-ቀመር ላይ ጫና በማሳረፍ የሚመለከቱትን በመቆጣጠር ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ ይህም ለተጽዕኖ ስራዎች ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ሲሉ ለየሕግ አውጭዎች መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ባይትዳንስ በተባለ ተቋም ባለቤትነት የተያዘውን ተወዳጅ መተግበሪያ ቤጂንግ “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር” መጠቀም ትችላለች፤ ይህም መሳሪያዎችን በቴክኒክ ለማላላት እድል ይሰጣታል ሲሉ ነው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ስጋቱን የገለጹት።
ለብሄራዊ ደህንነት ሲባል የውጭ ግዢዎችን የሚገመግመው የአሜሪካ መንግስት የውጭ ኢንቨስትመንት ኮሚቴ በፈረንጆቹ 2020 ባይትዳንስ የአሜሪካን መረጃ ቲክቶክን በመጠቀም ለቻይና መንግስት ሊያስተላልፍ ይችላል በሚል ፍራቻ ትእዛዝ አስተላልፏል ነው የተባለው።
ኮሚቴውና ቲክቶክ የመተግበሪያውን ከ100 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች መረጃ ለመጠበቅ የብሔራዊ ደህንነት ስምምነት ላይ ለመድረስ ለወራት ሲነጋገሩ ቆይተዋል።
የቲክቶክ ስራ አስፈፃሚ ቨኔሳ ፓፓስ በመስከረም ወር ላይ ለአሜሪካ ኮንግረስ እንደተናገሩት ቲክ ቶክ “የአሜሪካ የተጠቃሚ መረጃዎችን የበለጠ ለመጠበቅ እና የአሜሪካን ብሄራዊ ደህንነት ፍላጎቶች ሙሉ በሙሉ ለመፍታት ከአሜሪካ መንግስት ጋር የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጫፍ ላይ ነው” ብለዋል።
ዳይሬክተር ሬይ እንደተናገሩት የቻይና ኩባንያዎች የመንግስት መሳሪያ ሆነው በማገልገል መንግስት የሚፈልገውን ሁሉ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል፤ይህም የሚያሳስብ በቂ ምክንያት መሆኑን አስምረዋል።
የቲክቶክ ቃል አቀባይ ዳይሬክተር ሬይ እንደገለጹት የኤፍቢአይ ግብአት ከአሜሪካ መንግስት ጋር የምናደርገው ድርድር አካል ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ 2020 በአሜሪካ ውስጥ መተግበሪያው ጥቅም ላይ እንዳይውል ለማገድ ሞክረዋል።