የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ነዋሪዎች መንግስት ቀያቸውን ከሕወሃት ቁጥጥር ነጻ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ
ተፈናቃዮቹ የአበርገሌ፣ ዝቋላ፣ ዛታና ጻግብጂ ወረዳዎች በህወሃት ቁጥጥር ስር ናቸው ብለዋል
ሕወሓት ከተቆጣጠራቸው የዋግ ኽምራ ዞን ቦታዎች ከ61 ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ዞኑ አስታውቋል
በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን በህወሃት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ወረዳዎች ነዋሪዎች መንግስት ነጻ እንዲያወጣቸውና ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠየቁ፡፡
አሁን ላይ ከአበርገሌ፣ ከዝቋላ፣ ከዛታ፣ ከጻግብጂና ሰቆጣ ዙሪያ፣ ከኦፍላ ወረዳዎችና አላማጣ ከተማ የተፈናቀሉ ዜጎች ሰቆጣና ዝቋላ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በዞኑ አሁን ላይ 61 ሺ 668 ተፈናቃዮች እንዳሉ ዞኑ የገለጸ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የገቡት 18 ሺ 748 ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡ ምንም እንኳን ከ 18 ሺ በላይ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የገቡ ቢሆንም በመደበኛ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ግን ከ 2 ሺ በታች እንደሆኑም ዞኑ ገልጿል፡፡
ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ዝቋላ ወረዳ ደብረ ዓባይ አካባቢ ተፈናቅለው ጽጽቃ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጊዜአዊ መጠለያ ጣቢያ እንዳሉ የገለጹት ወ/ሮ ኪሮስ ወ/ሚካኤል ከቤታቸው ከወጡ ሁለት ወር እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ኪሮስ አሁን ላይ ያላቸው ንብረታት ስለተዘረፈባቸው ተስፋ መቁረጣቸውንና እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ወደቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ቢገልጹም እዛ ያለው ነገርም አሁን ካሉበት አለመሻሉ ጭንቀት ውስጥ እንከተታቸው ነው የገለጹት፡፡
ከዝቋላ ወረዳ ርዕሰ ገነት 06 ቀበሌ ተፈናቅለው ዕርዳታ ጠባቂ እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ ቄስ ምህረቱ ነጋ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት አካባቢያቸው በህወሃት ቁጥጥር ስር በመሆኑ ወደቀያቸው መመለስ አልቻሉም፡፡ መንግስት አካባቢውን የማያስለቅቅ ከሆነ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በመቆየት ዕርዳታ ጠባቂ ከመሆን ውጭ ምንም ምርጫ እንደሌላቸው ቄስ ምህረቱ ነጋ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም መንግስት በአፋጣኝ ህወሃትን አስለቅቆ ወደቀያቸው እንዲመልሳቸው አስተያየት የሰጡ ተፈናቃዮች ገልጸዋል፡፡
ሌሎች ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ተፈናቃዮች ደግሞ ከዕርዳታም በላይ ወደቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ገልጸው ይህንንም ለማድረግ መንግስት ህወሃትን እንዲያስለቅቅላቸው ጠይቀዋል፡፡
የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጸው መንግስት ወደቀያቸው እንዲመልሳቸው ጥያቄ ያቀረቡት በህወሃት ቁጥጥር ስር ካሉ ወረዳዎች ተፈናቅለው ሰቆጣ የገቡ ተፈናቃዮች ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የአበርገሌ፣ የዝቋላ፣ የዛታ፣ የጻግብጂና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ በመሆናቸው መንግስት ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጥያቄ እያቀረቡ እንደሆነም ዞኑ አስውቋል፡፡
ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየወጡ ያሉት ፎቶዎች በዞኑ ረሃብ መከሰቱን ያመለክታል የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች ይደመጣሉ፡፡ ይህንን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የዞኑ የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሱ “ረሃብ አለም የለም” ለማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ችግር ላይ ላለው ዞን እርዳታ የሚቀርቡ ድርጅቶች እንዳሉ ያነሱት አቶ ከፍያለው ዜጎቹ የሚያገኙትን እርዳታ ለማብሰልና በአግባቡ ለመመገብ ግን የመብራትና ተያያዥ ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ በመብራትና በወፍጮ አለመኖር ምክንያት ሕጻናትና እናቶች በየዕለቱ ሰዓቱን ጠብቀው ባለመመገባቸው ሰውነታቸው እንደተጎዳ ነው የተገለጸው፡፡
አሁን ላይ ይህ ችግር እየተከሰተ ያለው በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች በህወሃት ቁጥጥር ስር በመሆናቸው ነው ያለው ዞኑ መንግስት አካባቢዎቹን ከህወሃት ነጻ ማውጣት እንዳለበት ጠይቋል፡፡
የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እርዳታ ከሚመጣላቸው ወደቀያቸው መመለስን እንደሚመርጡም ተናግረዋል፡፡ ዜጎቹ ከሁሉም አይነት እርዳታዎች ውጭ ከሆኑ 17 ወራት የተቆጠሩት “ነጻ ባለመውጣታችን ነው” ም ብለዋል፡፡ የአበርገሌ፣ የዝቋላ፣ የዛታ፣ የጻግብጂና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች ነዋሪዎች የህወሃት ታጣቂዎች ንብረታቸውን መዝረፋቸውን፣ ታጣቂዎቹን ደግሞ እንዲቀልቡ ጥያቄ እየጠየቋቸውና እያስገደዷቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዋግ ኽምራ ዞን፤ አካባቢዎቹ በ 2011 ዓ.ም በድርቅ፣ በ2012 በአንበጣ፣ በ2013 ደግሞ በጦርነት በመቆየታቸው ችግሩ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ዞኑ፤ በህወሃት ከመያዙ አስቀድሞ 54 በመቶ የሚሆነው በቀጥታ ተረጂ የነበረ ሲሆን ከ3ዐ በመቶ በላይ ሕዝብ ደግሞ በሴፍቲኔት መርሃ ግብር የሚረዳ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ህወሃትን ማሸነፉን እና ከአማራ ክልል ማስወጣቱን ቢገልጽግም በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ 39 ቀበሌዎች በመንግስት በሽብር በፈረጀው የህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ዞኑ ገልጿል፡፡