ደሞዝ ያልተከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች አቤቱታቸውን እያቀረቡ ነው
ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በፊት የተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከትግራይ በተጨማሪ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል፤ ትምህርት እና የጤና ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የህዝብ መገልገያ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡
በርካቶች እጅግ ዘግናኝ ለሆኑ ሰብዓዊና ጾታዊ ጥቃቶች እንዲሁም ተወልደው ካደጉበት ቀዬ ለመፈናቀል ተገደዋል፡፡ አሁንም በጦርነቱ ዳፋ ምክንያት ከባድ ዋጋን እየከፈሉ ያሉ በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ሆኖም ሳለ ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ጦርነቱ ሶስቱንም ክልሎች ቀድሞ ከነበሩበት የሰላምም ሆነ የምጣኔ ሃብት ይዞታ ሌሎች እንቅስቃሴዎችም ውጭ ያደረገም ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል” ባሉለት በትግራይ ክልል መድሃኒት፣ ምግብ፣ ገንዘብ፣ የቴሌኮም እና የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸውን እንዲጀምሩም ተደጋጋሚ ጥያቀዎች ይቀርባሉ፡፡
በብዙዎቹ የክልሉ ከተሞች ባለው “ከፍተኛ” የትራንስፖርት እና የፋይናንስ ችግር ምክንያት በተለይ ከአመሻሽ ጀምሮ የሚታይ እምብዛም እንቅስቃሴ እንደሌለ ይነገራል፡፡ ለወትሮው በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ደምቃ ትታይ የነበረችው የክልሉ ርዕሰ ከተማ መቀሌ ጭር ስለማለቷም አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመቐለ ከተማ ነዋሪው አቶ ሰሎሞን ገ/ሚካኤል “የከተማዋ ሰው እጅጉን ፈታኝ ጊዜ እያሳለፈነው ”ይላሉ፡፡
“ሕዝቡ ኑሮ ከብዶታል፤ የሚከፈል ምንም አይነት ደሞዝ የለም፤ እርስ በእርስ በመተጋገዝ ላለፉት 8 ወራት ህይወትን ሲያስቀጥል ቆይቷል አሁን ግን ትንፋሹን ለማቆየት ለዘመናት ጥሮ ግሮ ያፈራውን ንብረት በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ እየተገደደ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አሁን ሰዎች ያላቸውን ነገር ሁሉ አሟጠው እየተጠቀመ መሆኑን ያነሱት ነዋሪው፤ ባለው ነገር ሌሎችን ሲያግዝ የነበረው ሰው አሁን ላይ ወደ ተረጅነት ደረጃ እንደደረሰም ነው ለአል ዐይን አማርኛ የገለጹት፡፡
“አሁን ነገሮች እጅግ ከባድ እየሆኑ ነው” የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ሰዉ በእጁ ላይ ብር ስለሌለው “የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በረሃብ ምክንያት ቤቱን ዘግቶ ራሱን የሚያጠፋበት አሳዛኝ ዜና መስማት የተለመደ ሆኗል” ሲሉም ነው አሁን ያለውን ችግር የሚያስቀምጡት፡፡
በክልሉ ካለው ችግር ጋር ተዳምሮ በሸቀጦች ዋጋ ላይ የሚስተዋለው ጭማሪ ኑሮውን “እጅግ ከባድ” ከማድረግም በላይ ነዋሪውን ለከፍተኛ ጭንቀት ዳርጎታል፡፡ ይህ በመሆኑ ነዋሪው መንገድ ላይ የእጅ ስልኩን ጨምሮ ሌሎች የቤት ንብረቶቹን እንዲሁም፤ አርሶ አደሩ እንደ ህይወቱ የሚሳሳለቸውን እንስሳቱን መሸጥ ጀምሯል፤ እንደ ግለሰቡ ገለጻ፡፡
ደሞዝ ያልተከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች
በጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ እየተከፈላቸው አይደለም፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር ለአል ዐይን አማርኛ በላኩት የኢሜይል መልዕክት በትግራይ ክልል የዩኒቨርሲቲ ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች እያሳለፉት ያለው ህይወት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
7 ሺ የሚሆኑ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች አሁን ላይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉም መምህሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ያለ ደመወዝ የቆዩት የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ህይወት መክበዱን ተከትሎ ትንሽ ብር እንኳ ማግኘት ትልቅ ነገር ሆኖባቸው በአሁኑ ወቅት 100 እና 200 ብር እንኳ ማግኘት በማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል እንደ መምህሩ ገለጻ፡፡
መምህሩ፤ የትምህርት ሚኒስቴር ለችግሩ መፍትሄ በማፈላለግ ኃላፊነቱ ሊወጣ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡ ሆኖም ሚኒስቴሩ፤ ከትግራይ ክልል የወጡ መምህራንን ወደ ሌላ ተቋማት ከማሸጋገር በዘለለ ሊያደርግ የሚችለው ምንም ዐይነት ነገር እንደሌለ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
እንደ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ሁሉ በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ 47 ሺ መማህራን፣ 10 ሺ የአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች፣ በ 10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሀኪሞች፣ የባንክ ሰራተኞች እና ሌሎች በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የመንግስት ሰራተኞች ላለፉት ስምንት ወራት ደመወዝ አልተከፈላቸውም ተብሏል፡፡
አላማጣ- የተቸገሩ ሰዎች መናከሪያ
አል ዐይን አማርኛ ባገኘው መረጃ መሰረት አዲስ አበባም ሆነ በውጭው ዓለም ለሚኖሩ ዘመዶቻቸው ስልክ ለመደወልና ገንዘብ እንዲልኩላቸው ለመጠየቅ ወደ አላማጣ የሚመጣ ሰው በርካታ ነው፡፡ ከመሃል ትግራይ ወደ አላማጣ እየመጣ ያለው ሕዝብ ከአቅም በላይ በመሆኑ በየበረንዳው፣ በቤተ ክርስቲያናት፣ በመስጂዶች ፣ በመኪና ጋራዦች እና በስታዲየም ሲውል ሲያድር መመልከት የተለመደ መሆኑንም ምንጮች ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
ሰዎች ወደ አላማጣ የሚሄዱት ስልክ ለመደወል ብቻ ሳይሆን ወደ ቆቦና ሌሎች አካባቢዎች ለመሄድም ጭምር እንደሆነ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ወደ ቆቦ ከሚገቡት የትግራይ ተወላጆች መካከል የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መታወቂያ ያላቸው እንዳሉበት የተገለጸ ሲሆን እነርሱም አዲስ አበባን ጨምሮ ወደፈለጉበት ቦታ እንዲሄዱ ይፈቀድላቸዋል ተብሏል፡፡ ከትግራይ ክልል ወደ ሰሜን ወሎ ዞን የመጡና የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መታወቂያ የሌላቸው ዜጎች ወደ መጠለያ ካምፕ እንዲገቡ እየተደረገ እንደሆነም ነው መረጃዎቹ የሚያመለክቱት፡፡
የቆቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰኢድ አባተ ከቀናት በፊት ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት፤ በሰሜን ወሎ ዞን ከመሀል ትግራይ፤ ከራያ አላማጣ ከአላማጣ ከተማ፣ ከራያ ባላ እና ከሌሎች አካባቢዎች በርካታ ተፈናቃዮች እየመጡ መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ከመሀል ትግራይ ከ500 በላይ ተፈናቃዮች ቆቦ ከተማ መግባታቸው ተሰምቷል።
አስተያየታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ የሰጡ የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች የተፈናቃዮች መበራከት ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል። የቆቦ ከተማ “ዳግም ወደ ጦርነት እንዳትመለስና ውድመት እንዳይከሰት ስጋት አለን” የሚሉት ነዋሪዎቹ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የጉዳዩን አሳሳቢነት በትኩረት እንዲመለከቱትም ጠይቀዋል፡፡
አሁን ላይ በክልሉ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ እርዳታ ጠባቂ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራምን እና የዓለም ጤና ድርጅትን መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት አስታውቀዋል፡፡
ተቋማቱ በክልሉ ሰብዓዊ እርዳታዎች ባልተገደበ ሁኔታ እንዲቀርቡ መጠይቃቸውም ይታወሳል፡፡
ምግብ ነክ እቃዎችን የጫኑ 20 እንዲሁም ነዳጅ የጫኑ 3 ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀሌ መንቀሳቀስ ጀምረዋል ያለው መንግስት የክልሉን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ከፍ ለማድረግም በየቀኑ 40 የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ እንዲገቡ የሚደረግ ይሆናል ሲል ትናንት ማስታወቁም አይዘነጋም።