“ህወሓት፤ በአማራ ክልል የጦር ወንጀል መፈጸሙን የሚሳይ ማስረጃዎች እየጨመሩ ነው” አምነስቲ
ህወሓት በሰነድ የተያዙትን ጨምሮ ሌሎች ግፎችን መፈጸሙን እንዲያቆም ጠይቋል
ቡድኑ፤ ክብር የሚነኩ አጸያፊ ስድቦችን፣ የግድያ ዛቻዎች እንዲደርሱ አድርጓልም ተብሏል
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት ታጣቂዎች በአማራ ክልል የጦር ወንጀል መፈጸሙን የሚያሳዩ ማስረጃዎች እየጨመሩ መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የመብት ተሟጋች ተቋም አስታወቀ።
ተቋሙ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ህወሃት በአማራ ክልል ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች የጦር ወንጀል መፈጸሙን አስታውቋል።
ይህ ህወሃት ፈጽሞታል የተባለው ወንጀል በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል የመሆን ዕድልም እንዳለው ነው መግለጫው ያስታወቀው። መግለጫው የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች በስፋት መፈጸማቸውንና በንጹሃን ላይም ግድያ መፈጸሙን አካቷል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድና ግሬት ሌክስ አካባቢ ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን የህወሓት ኃይሎች በስፋት የአስገድዶ መድር ጥቃቶችን፣ ግድያዎችን እና ከሆስፒታል ሳይቀር ዝርፊያ መፈጸማቸውን አስታውቀዋል።
አምነስቲ የህወሓት ታጣቂዎች ሆን ብለው በርካቶችን መግደላቸውን፣ በርካታ ሴቶች መደፈራቸውን የገለጸ ሲሆን፤ 14 ዓመት የሚሆናቸው ልጆም መደፈራቸውን ገልጿል።
አምነስቲ እንዳለው በአማራ ክልል ግፍ የተፈጸመው በነሃሴ እና በመስከረም ሲሆን፤ ድርጊቱም በቆቦ እና በጭና መፈጸሙን አምነስቲ በሪፖርቱ አመላክቷል።
አምነስቲ “የህወሓት ኃይሎች፤ መሰረታዊ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎችን ፍጹም የማሳነስ ተግባር ፈጽመዋል” ብሏል።
የህወሃት ታጣቂዎች በቆቦ እና አካባቢው ነዋሪዎች ላይ ካደረሷቸው ግድያዎች፣ አስገድዶ መድፈርና ሌሎች ከአካላዊ ጉዳት ባለፈም ክብር የሚነኩ አጸያፊ ስድቦችን፣ የግድያ ዛቻዎችን ማድረሳቸውም ተገልጿል።
የህወሃት አመራር በአስቸኳይ “በሰነድ የያዝናቸውን ጨምሮ ግፍ መፈጸሙን እንዲያቆም እና እንዲህ አይነት ወንጀል የፈጸሙ አባላቱን ማስወጣት አለበት” ብሏል።