ህወሃት ከያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በቀን ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች እየተፈናቀሉ መሆኑ ተገለፀ
ከፍተኛ ባለስልጣናት በሰሜን ወሎና በዋግ ኽምራ ላለው የተፈናቃይ ጉዳይ ሊያስቡ ይገባል ተብሏል
ከ”መሃል ትግራይ” “የተፈናቀሉ ዜጎች ቆቦ ከተማ ገብተዋል ተባለ
በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ከሚገኙና በህወሃት ቁጥጥር ስር ከሚገኙ አካባበ ዎች በቀን በአማካይ እስከ 2 ሺ ተፈናቃዮች ወደ ሰቆጣ እየመጡ መሆኑን ዞኑ አስወቁ።
በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ የሚገኙት አበርገሌ፣ ፃግብጅ፣ ዛታ፣ ዝቋላና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች አሁንም በመንግስት ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው ህወሃት ቁጥጥር ስር መሆናቸውን አል ዐይን አማርኛ ከዞኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከአበርገሌ፣ ከፃግብጅ፣ ከዛታ፣ ከዝቋላና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች እንዲሁም ከኮረም እና ከአለማጣ ወረዳዎች በየቀኑ በአማካይ 2 ሺህ ተፈናቃዮች ወደ ሰቆጣ ከተማ እየመጡ መሆኑም ተገልጿል። አሁን ላይ በብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ ያለው ተፈናቃይ ቁጥር ከ52 ሺህ በላይ መድረሱም ተገልጿል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽ/ቤት በዞኑ ሦስት መጠለያ ጣቢየዎች ተዘጋጅተው በዝቋላ መጠለያ ጣቢያ 18 ሺህ 304 ፣ በወለህ መጠለያ ጣቢያ 10 ሺህ 15 ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቋል።
ከፍተኛው የተፈናቃይ ቁጥር በሰቆጣ መጠለያ እንዳለ የገለጸው ጽህፈት ቤቱ፤ እስካሁን ድረስ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነም ጠቅሷል።
ይሁንና የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የታሸጉና በዱቄት መልክ የተዘጋጁ አልሚ ምግቦች፣ የምግብ ማብሰያ እቃዎች ፣ የጥራጥሬ እህሎች፣ የመኝታ፣ የመጠለያ እና የተለያዩ አልባሳትን ለተፈናቃዮቹ ሰጥተዋል ተብሏል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደስታዬ ጌታሁን በየጊዜው በርካታ ተፈናቃዮች እየመጡ መሆኑን ገልጸው፤ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልግና ለዚህም በቀጣይ ሀብት የማፈላለግ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ተፈናቃይ ዜጎች ወደየመጡበት አካባቢ ተመልሰው የቀደመ ኑሯቸውን በሰላም እንዲመሩ የሚደረግበት ሁኔታ ካልተመቻቸ ችግሩን መቋቋም እንደማይቻልም አቶ ደስታዬ ተናግረዋል።
ከዋግ ኽምራ ዞን በተጨማሪም በሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንደሚገኝ የቆቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰኢድ አባተ ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት ከመሀል ትግራይ፤ ከራያ አለማጣ ከአለማጣ ከተማ፣ ከራያ ባላ እና ከሌሎች አካባቢዎች በርካታ ተፈናቃዮች እየመጡ እንደሆነ ተገልጿል።
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ከመሀል ትግራይ 297 ወንዶችና 55 ሴቶች በድምሩ 352 ተፈናቃዮች ቆቦ ከተማ መግባታቸው ተሰምቷል።
አስተያየታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ የሰጡ የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ አሁን ላይ የተፈናቃዮች መበራከትና አሁን ያለው ሁኔታ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ተናግረዋል።
የቆቦ ከተማ ዳግም ወደ ጦርነት እንዳትመለስና ውድመት እንዳይከሰትም ስጋት እንዳላው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የጉዳዩን አሳሳቢነት በትኩረት እንዲመለከቱትም ዞኑ ጥያቄ አቅርቧል።