ጉዳት የደረሰበት ሳዲዮ ማኔ በሴኔጋል የዓለም ዋንጫ ቡድን ውስጥ ተካተተ
የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን የመክፈቻ ጨዋታውን በህዳር 20 ከአዘጋጇ ኳታር ጋር የሚያደርግ ይሆናል
አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ የማኔ ሁኔታ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይሻሻላል የሚል ተስፋ አለኝ ብሏል
ሳዲዮ ማኔ በቅርቡ ጉዳት ቢያጋጥመውም በሴኔጋል የዓለም ዋንጫ ቡድን አባል በመሆን በአሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ ተመርጧል።
የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ የባየር ሙኒክ አጥቂ ሁኔታ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይሻሻላል የሚል ተስፋ እንዳለውም ተናግሯል።
“ጉዳቱ ቀዶ ጥገና እንደማያስፈልገው እምነት አለኝ”ም ብሏል አሰልጣኙ።
ሳዲዮ ማኔ ማክሰኞ እለት ክለቡ ባየርን ሙኒክ ቨርደር ብሬመንን 6-1 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ በጉዳት ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ በውድድሩ ላይ ያለው ተሳትፎ አጠራጣሪ እንዳደረገው አይዘነጋም።
የ30 አመቱ ወጣት የደረሰበት የጅማት ጉዳትን ተከትሎ ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውጭ እንደሆነም ነበር ደይሊ ሜይል በወቅቱ L'Equipeን ጠቅሶ የዘገበው።
ይሁን እንጅ የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኙ ሲሴ “ማኔን በቡድኑ ውስጥ ማቆየት እመርጣለሁ” ሲል ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
“ሳዲዮ ማኔ በቡድናችን ውስጥ ወሳኝ ተጫዋች ነው፤ በሁለት ወይም ሶስት ሳምንታት ውስጥ ለውጥ እንደሚኖር ተስፋ በማድረግ ጉዳቱን መከታተል መቀጠል አስፈላጊ ነው፤ እኛ ግን በእውነት ተስፈኞች ነን”ም ነው ያለው ሲሴ።
አክሎም “ሳዲዮ ማኔ እንዲያገግም ለማድረግ ሁሉንም አስፈላጊ ዘዴዎች እንጠቀማለን” ብሏል፡፡
የሰኔጋል ብሄራዊ ቡድን ኔዘርላንድስ፣ ኢኳዶር እና ኳታር በሚገኙበት ምድብ 1 ላይ መደልደሉ ይታወቃል፡፡
በዚህም መሰረት ቡድኑ የመክፈቻ ጨዋታውን በህዳር 20 ከአዘጋጇ ኳታር ጋር እንዲሁም በቀጣይ ከኔዘርላንድ እና ኢኳዶር ጋር የሚገናኝ ይሆናል።
ያም ሆኖ የሳዲዮ ማኔ ጉዳት የዓለም ዋንጫ በይፋ ሊጀመር ጥቂት ሳምንታት ሲቀረው የተከሰተ እንደመሆኑ ለብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ እና መላ ሴኔጋላዊያን አስደንጋጭ ዜና እንደሆነ ነው፡፡
የማኔ አለመኖር በሴኔጋል ካምፕ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርምም ነው የተባለው፡፡
ማኔ እስካሁን በርካታ ዋነወጫዎችን ያነሳ እና 34 ጎሎችን በስሙ ያስቆጠረ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ሰኔጋላዊው ኮከብ ሀገሩ የዘንድሮውን አፍሪካ ዋንጫ እንድታነሳ የነበርው ከፍተኛ ሚናም አይዘነጋም፡፡
በክረምቱ በ35 ሚሊየን ፓውንድ ከሊቨርፑል ባየርን የተቀላቀለው ማኔ በጀርመን ባሳለፈው የመጀመርያ የውድድር ዘመን ለክለቡ ድንቅ ብቃት ማሰየት የቻለ ተጫዋችም ነው፡፡
በሁሉም ውድድሮች 23 ጨዋታዎችን አድርጎ 11 ጎሎችን በማስቆጠር አራት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችንም አመቻችቷል።