ሩሲያና አሜሪካ የእስረኛ ልውውጥ አደረጉ
አንድ ለአንድ እስረኛ ልውውጡ በአለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ነጋዴው ቪክቶር ቦወት እና የአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ብሪትኒ ግሪነርን ተደርጓል
ልውውጡ የተካሄደው በአቡ ዳቢ ሲሆን ቦወት ወደ ሀገር ቤት መመለሱን ሩሲያ አረጋግጣለች
ሩሲያ የአሜሪካ የሴት ቅርጫት ኳስ ኮከብ ብሪትኒ ግሪነርን "አስደናቂ" በተባለ የከፍተኛ የእስረኞች ልውውጥ መፍታቷን የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ይህ ልውውጥ ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፍተኛ ግብ አሳክቷልም ተብሏል።
ከሩሲያ ጋር በስምንት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ የተደረገው ይህ ልውውጥ በውጭ አገር የታሰሩትን ታዋቂ አሜሪካውያንን ከእስር እንዲፈቱ አድርጓል።
ግሪነር የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ስትሆን፤ በአደንዛዥ ዕፅ ክስ ለወራት በእስራት ቆይታለች።
በአንድ ለአንድ እስረኛ ልውውጡ አለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ነጋዴው ቪክቶር ቦወት ተለቋል።
“የሞት ነጋዴ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠውን ሩሲያዊ ለመልቀቅ የተስማማው የባይደን አስተዳደር ግሪነርን ወደ ሀገሯ ለመመለስ ያጋጠማትን ከፍተኛ ጫና አጉልቶ አሳይቷል ሲል አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የግሪነርን መፈታት ለማረጋገጥ ፕሬዝዳንቱ ቦወት እንዲፈታ ያዘዙ ሲሆን፤ የቦወትን የ25 ዓመት የፌደራል እስራት እንዲቋረጥ ትእዛዝ ፈርመዋል።
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ልውውጡን አረጋግጧል። የሩሲያ የዜና አገልግሎት በሰጠው መግለጫ ልውውጡ የተካሄደው በአቡ ዳቢ ሲሆን ቦውት ወደ ሀገር ቤት መመለሱን አረጋግጧል።