የስፔኑ ንጉስ ዩዋን ካርሎስና የግብፅ ንጉስ ፉአድ 2ኛን ጨምሮ በርካታ ንጉሳውያን በትምህርት ቤቱ ተምረዋል
በስዊዘርላንድ የሚገኘው “ኢኒስቲትዩት ሊ ሮሰይ” ትምህርት ቤት የዓለማችን ውዱ ትምህርት ቤት መባሉ ተነግሯል።
ስዊዘርላንድ የዓለማችን ውድ ትምህርት ቤቶች መገኛ ስትሆን፤ በሀገሪቱ ሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪን በዓመት ከ75 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚያስከፍሉ ይነገራል።
ከእነዚህም ውስጥ “ኢኒስቲትዩት ሊ ሮሰይ” የተባለው በእጅጉ ውዱ ትምህርት ቤት የተባለለት የሚገኝ ሲሆን፤ በትምህርት ቤቱ ለመማር አንድ ተማሪ በዓመት 130 ሺህ ዶላር ወይም 6 ሚሊየን 630 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይጠበቅበታል።
የአዳሪ ትምህርት ቤት የሆነው “ኢኒስቲትዩት ሊ ሮሰይ”፤ የንጉሳውያንተ ትምህርት ቤት በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ የስፔኑ ንጉስ ዩዋን ካርሎስ፣ የግብፅ ንጉስ ፉአድ 2ኛ፣ እና የቤልጂየሙ ንጉስ አልበርት 2ኛ የዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደነበሩ ይነገራል።
በፈረንጆቹ በ1880 በፓውል ካርናል የተመሰረተው ትምህርት ቤቱ፤ ሁለት ካምፓሶች ያሉት ብቸኛ ትምህርት ቤት እንደሆነ ይነገርለታል።
ትምህርት ቤቱ የኦሎምፒክ መጠን የመዋኛ ገንዳ፣ የሜዳ ቴኒስ መጫወቻ፣ የመሳሪያ ተኩስ መለማመጃ፣ የፈረስ መጋለቢያ፣ እና 40 ሚሊየን ዩሮ የወጣበት የኮንሰርት አዳራሽ በውስጡ የያዘ ነው።
የተማሪዎች እና የመምህራን ምጣኔው ሲታይም ለ420 ተማሪዎች 150 መምህራን የተመደቡ ሲሆን፤ በአንድ የመማሪያ ክፍል ውጥም በአማካኝ ከ10 ያነሱ ተማሪዎች ነው የሚማሩት ተብሏል።
ራሱን ዓለም አቀፍ ትምርት ቤት ነኝ የሚለው “ኢኒስቲትዩት ሊ ሮሰይ” በዓመት ከሚቀበላቸው አጠቃላይ ተማሪወች ውስጥ ከአንድ ሀገር 10 በመቶውን ብቻ ነው የሚወስድ መሆኑን ታውቋል።
በዓመት ከሚቀበላቸው 420 ተማሪዎችን ውስጥ እድሜያቸው ከ7 እስከ 18 መካከል የሚገኙ 30 የተቋሙ መምህራን ልጆችን በነጻ ሚቀበል መሆኑም ተነግሯል።
በየዓመቱ 3 ነጻ የትምህርት እድሎችን የሚሰጠው ትምህርት ቤቱ፤ ቀሪዎቹ ተማሪዎች ግን በዓመታዊው የ130 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከፍያ ነው የሚቀበለው ተብሏል።