ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ "ለትኩረት" ሲባል አራት ኮሌጆችን ሊዘጋ ነው መባሉን መምህራን ተቃወሙ
ዩኒቨርሲቲው “ልየታ” ላይ ለማተኮር ከአማርኛ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህልና እና ሀገር በቀል እውቀቶች ጋር የተያያዙ የትምህርት ክፍሎችን ለመዝጋት ማሳወቁን መምህራን ተናገሩ
ትምህርት ሚንስቴር ዩኒቨርሲቲው "በትኩረትና ተልዕኮ" ልየታው መዝጋት "መብቱ" ነው ብሏል
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቀጣይ የትኩረቴ አቅጣጫ አይደሉም ያላቸውን አራት ኮሌጆች ሊዘጋ ነው ሲሉ መምህራን አቤቱታ አቅርበዋል።
- የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ያላለፉ ተማሪዎች እጣፋንታ ምን ይሆናል?
- የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 40 በመቶ ብቻ ማለፋቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
ዩኒቨርስቲው ሰኔ መጨረሻ ላይ በስብሰባ አሳውቆናል ያሉት መምህራን "በልየታ እና በልህቀት ማዕከል" ያልተካተቱ ናቸው ያላቸውን ማህበራዊ፣ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ፣ ህግና የስነ ትምህርት ኮላጆችን ሊዘጋ ነው ብለዋል።
መምህራኑ ዩኒቨርሲቲው ለዓመታት ያስተማራቸውንና ሀብቱን ያፈሰሰባቸውን አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ ከባህል እና ከሀገር በቀል እውቀቶች ጋር የተያያዙ 18 ትምህርት ክፍሎችን ሊዘጋ ነው በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ሲከፈት የተጀመሩ ትምህርቶችና በሰው ኃይል የደረጁ የትምህርት ክፍሎች መዘጋታቸው አሳዝኖናል ብለዋል።
በእንግሊዘኛ ትምህርት ክፍል የስነ-ጽሁፍ መምህር የሆኑት መዘምር ግርማ፤ የዩንቨርስቲው "የልህቀት ማዕከል" ለመሆን አያስፈልጉም ያላቸውን፤ ነገር ግን 32 ፕሮግራም ያላቸውን የትምህርት ክፍሎች ለመዝጋት መወሰኑን "አምባገነን" ብለውታል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሦስት ዓመታት በእነዚህ ትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችን ላለመቀበል ውስጥ ውስጡን ሰርቷል ሲሉ የሚከሱት መምህሩ፤ የዩኒቨርሲቲው አሻራ እየጠፋ ነው ብለዋል።
ይዘጋሉ ከተባሉ ፕሮግራሞች አንዱ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ (ፒ.ኤች.ዲ) ድረስ የሚያስተምረው የዘርዓ ያቆብ የመካከለኛው ዘመን ጥናት ማዕከል እንደሚገኝበት መዘምር ግርማ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በየዓመቱ ጉባኤ የሚያካሂደው ባህል ማዕከሉም ደጆቹ ከሚዘጉ የደብረ ብርሀን ዩኒቨርስቲ ተቋማት መሀል ሆኗል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከሚቋቁሙበት ሦስት ዓላማ ውስጥ ጥናትና ምርምርና የማህበረሰብ ግልጋሎት የመስጠት ኃላፊነቱን ደብረ ብርሀን ዩኒቨርስቲ መዘንጋቱን ያሳያል ይላሉ።
ቢዚህ የሚስማሙትና ሌላው አል ዐይን ያነጋገራቸው የዩንቨርስቲው መምህር ዶ/ር አዲሱ ኃይሉ እርምጃው ዛሬ እንደቀላል ቢታይም ነገ ዋጋ የሚያስከፍል ነው ባይ ናቸው።
ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል መሆኑን እንደማይቃወሙ የሚገልጹት መምህሩ፤ ሆኖም አካሄድና አሰራሩ ግን ቆም ተብሎ መታየት እንደሚገባው ተንግረዋል።
"የልህቀት ማዕከል መሆን ማለት ሌላውን መዝጋት ሳይሆን ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው። አካባቢዬን፤ አቅሜን አይቼ ያዋጣኛል የምለውን መንገድ ስሄድ ሌላውን መዝጋት ሳይሆን፤ ሌላውንም አቅፎ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይኖራሉ ማለት ነው" በማለት ውሳኔውን “የማይዋጥ” ብለውታል።
ዩኒቨርሲቲው "በልየታ እና በልህቀት ማዕከል" የመረጣቸው ዘርፎች ቢዝነስ፣ ጤናና ግብርና መሆናቸው ተነግሯል።
እነዚህ ዘርፎች አካባቢውን ያላጤኑና በዩኒቨርሲቲው አነስተኛ የሰው ኃይል ያላቸው ናቸው የሚሉት ዶ/ር አዲሱ፤ የዩኒቨርሲቲውን አቅምና ታሪካዊ ዳራ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብለዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ መምህራን እጣ ፈንታ ደጃቸውን ከሚዘጉ የትምህርት ክፍሎች ጋር የተሳሰረ ነው።
የደብረ ብርሀን ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ተዘጉ የተባሉ ኮሌጆችን ተጠይቀው "ውሸት" ነው ብለዋል።
“አራት ኮሌጅ ዘግተንም አናውቅም፤ አላሰብንም። ውሸት ነው፤ አልሆነም” ሲሉ የመምህራኑን ቅሬታ አስተባብለዋል።
ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በላይ እንዲያብራሩ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም።
ጉዳዩ አንገብግቦናል ያሉ የዩኒቨርስቲው 20 የሚሆኑ መምህራት አራት ገጽ ያለው አቤቱታ ትምህርት ሚንስቴርን ጨምሮ ለተለያዩ ተቋማት አስገብተዋል።
ስለ ጉዳዩ አል ዐይን የጠየቀው ትምህርት ሚንስቴር፤ ዩኒቨርስቲው "በትኩረትና ተልዕኮ" ልየታው አራት ኮሌጅ ብቻ ይበቃኛል ካለ "መብቱ" ነው ብሏል።
የትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ብዝኃ ኢኮኖሚ ለመፍጠር በያዘው ውጥን "ዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው ፕሮግራም ልክ አይቀጥሉም"በማለት የሚዘጉ፣ የሚታጠፉና የሚዘዋወሩ ትምህርት ክፍሎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
ሚንስትር ዴኤታው ደብረ ብርሀን ዩኒቨርስቲ በልየታ እርምጃው "ፋና ወጊ" መሆኑን ጠቅሰው፤ "ለሀገር ሲባል" የመረጠውን ማስተማር ይችላል ብለዋል።
ትምህርት ሚንስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ባለፉት ዓመታት ሁሉንም ዘርፍ በማስተማራቸው የጎደለው ሰፊ ነው ይላል።
በመሆኑም የትምህርት ተቋማቱን ለአምስት ከፍሎ በልየታ እንዲያስተምሩ በ2016 ሰፊ ስራ እሰራለሁ ብሏል።