4ኛው የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ትብብር ለዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ጉባኤ በባህሬን እየተካሄደ ነው
አረብ ኤምሬትስ፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ እና ባህሬን ቀጠናዊ የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጎልበት በጋራ በመስራት ላይ ናቸው
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮም ይህን የትብብር ማዕቀፍ ተቀላቅላለች
4ኛው የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ትብብር ለዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ጉባኤ በባህሬን መካሄድ ጀምሯል።
በማናማ እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ሞሮኮ በአዲስ አባልነት ተቀላቅላ እየተሳተፈች ነው።
አረብ ኤምሬትስ፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ እና ባህሬን በግንቦት ወር 2022 ቀጠናዊ የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጎልበት በአቡዳቢ የትብብር ማዕቀፍ አቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸው ይታወሳል።
የሞሮኮ የትብብር ማዕቀፉን መቀላቀልም ቀጠናዊ የኢንዱስትሪ ትብብርን እንደሚያሳድግ ታምኖበታል።
በማናማው ጉባኤ ንግግር ያደረጉት የግብጽ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አህመድ ሳሚር በአለም ብሎም በአረቡ አለም ላጋጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የዘላቂ ልማት እቅድ በማውጣት መስራት ይገባል ብለዋል።
አምስት ሀገራትን ያቀፈው የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ትብብር ለዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት የትብብር ማዕቀፍም የአረብ ሀገራትን ትስስር እያሳደገ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።
የአረብ ኤምሬትሱ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ይፋ ያደረጉት የትብብር ማዕቀፍ በኢንዱስትሪ፣ በምግብ፣ ጤና፣ ኢነርጂ እና ሌሎች ዘላቂ እድገትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች አባል ሀገራቱ ተቀራርበው እንዲሰሩ እድል ፈጥሯል።
የአባል ሀገራቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሮች በተሳተፉባቸው የትብብር ማዕቀፉ ጉባኤዎችም በተለያዩ የኢንቨስተመንት ፕሮጀክቶች በጋራ መስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈራረማቸው ይታወሳል።
በባህሬኑ ጉባኤም በብረታብረት፣ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እና ምግብ ነክ ዘርፎች አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ስምምነቶች እንደሚፈረሙ ይጠበቃል።