አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ 5 ተጨማሪ የዓለማችን ሀገራት የሻንጋይ ትብብር ድርጅትን ተቀላቀሉ
ግብጽ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ኳታር ፣ ባህሬን እና ኩዌት ድርጅቱን በአጋርነት ተቀላቅለዋል
የምስራቅ ሀገራት ስብስብ የሆነው የሻንጋያ ትብብር ድርጅት ዓመታዊ ጉባኤ በኡዝበኪስታን ተካሂዷል
በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት የሚመራውን የዓለም ተጽዕኖ ለመመከት የተቋቋመው የሻንጋይ ትብብር ድርጅት ዓመታዊ ጉባኤውን በኡዝበኪስታን አካሂዷል።
በሳመርካንድ ከተማ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ የቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ኢራን፣ ቱርክ እና ሌሎችም ሀገራት ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሳትፈውበታል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ድርጅቱን በአጋርነት ተቀላቀሉት የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ግብጽ፣ ኳታር ፣ ባህሬን እና ኩዌት እንኳን ደህና መጡ ብለዋል።
ቤላሩስን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን ሀገራት ወደዚህ ድርጅት ለመቀላቀል ፍላጎት እያሳዩ ሲሆን ኢራን በይፋ ድርጅቱን መቀላቀሏም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የሻንጋይ ትብብር ድርጅት የዓለምን ችግር ለመፍታት የተቋቋመ እንጂ ቡድን የመመስረቻ መድረክ አይደለም ብለዋል።
ለዓብነትም ድርጅቱ የዓለም ምግብ ችግሮችን፣ ሽብርተኝነትን እና የህይል እጥረቶችን ለመፍታት ይሰራል ሲሉም ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለዋል።
በአፍሪካ፣እስያ እና ደቡብ አሜሪካ ሀገራት መካከል በራሳቸው በብሄራዊ የመገበያያ ገንዘባቸው ሰፊ የንግድ ልውውጥ መፍጠር የድርጅቱ ዋነኛ አላማ እንደሆነም ተገልጿል።
ሞስኮ በዩክሬን በጀመረችው ጦርነት ምክንያት ማዕቀቦች እንደተጣሉባት የገለቱት ፕሬዝዳንት ፑቲን ከ300 ሺህ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ያለምንም ክፍያ ለታዳጊ ሀገራት እንደምታሰራጭም ተናግረዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ በበኩላቸው ቤጂንግ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩዋን እርዳታ ለታዳጊ ሀገራት የሰብዓዊ ድጋፎችን እንደምታደርግ በጉባኤው ላይ ገልቷል።
ሻንጋይ የትብብር ድርጅት በፈረንጆቹ 2001 ላይ በቻይናዋ ሻንጋይ የተቋቋመ ሲሆን ኡዝቤኪስታን፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ታጂኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ እና ካዛኪስታን ደግሞ መስራች ሀገራት ናቸው።
አፍጋኒስታን፣ ኢራን፣ ቤላሩስ እና ሞንጎሊያ በታዛቢነት ድርጅቱን የተቀላቀሉ ሲሆን አርመኒያ፣ አዛርባጂያ፣ ቱርክ፣ ስሪላንካ፣ ቻምቦዲያ እና ኔፓል ደግሞ ድርጅቱን ለመቀላቀል በሂደት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።
ከዓለማችን ህዝብ ቁጥር ውስጥ ግማሽ ገደማ የሖነው በዚህ ድርጅት ውስጥ በመደራጀት ላይ ሲሆኑ የድርጅቱ ሊቀመንበርነትን አባል ሀገራቱ በዙር እየመሩት ይገኛሉ።
የኡዝቤኪስታን ፕሬዝዳንት ሻቭካት ሚርዚቭ የወቅቱ የሻንጋይ የትብብር ድርጅትን በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ ይገኛሉ።