ኤምሬትስ በባለብዙ ወገን አለማቀፍ ትብብር ዙሪያ ምን ፖሊሲ ትከተላለች?
ሀገሪቱ ተለዋዋጭ የሆነው የአለም ማህበረ-ፖለቲካ ሁኔታ በባለብዙ ወገን ግንኙነትና ውይይት እንደሚፈታ ታምናለች
ኤምሬትስ የብሪክስ አባል እንዲሆኑ ከተመረጡ ስድስት ሀገራት መካከል አንዷ ሆናለች
የአረብ ኤምሬትስ ለአለም ሰላምና ደህንነት በጋራ ይሰራል ብላ በምታምንበት የብሪክስ ስብስብ አካል እንድትሆን ተመርጣለች።
በ2021 የብሪክስ ልማት ባንክን የተቀላቀለችው አቡ ዳቢ ከብሪክስ ጋር ለአመታት የዘለቀ ግንኙነት አላት።
የብሪክስ ወዳጅ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰኔ ወር 2023 በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን ልካለች።
በጆሃንስበርግ እየተካሄደ ባለው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤም ሚኒስትሮችን መላኳን የሚገልጸው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፥ ኤምሬትስ እንደ ብሪክስ ካሉ ቡድኖች ጋር ትብብሯን ትቀጥላለች ብሏል።
በቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ ደጋግማ የተሳተፈችው ኤምሬትስ በህዳር ወር 2023 የአለማቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (2023) ታስተናግዳለች።
ባለብዙ ወገን አለማቀፍ ተቋማት በተለይ የታዳጊ ሀገራትን ፍላጎቶች የሚመልሱ፣ ሰላም እና ደህንነት የሚያረጋግጡ እንዲሁም ልማትን የሚያስፋፉ እንዲሆኑም ድጋፏን ትቀጥላለች ብሏል ሚኒስቴሩ።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዋናነት ዘላቂ የኢኮኖሚ ብልጽግናን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል።
ተለዋዋጭ የሆነው የአለም ማህበረ-ፖለቲካ ሁኔታ እና ልዩነቶችም በባለብዙ ወገን ግንኙነት እና ውይይት እንደሚፈታ ነው ሀገሪቱ የምታምነው።
ለዚህም የበለጸጉት ብቻ ሳይሆን የታዳጊ ሀገራት ተሳትፎ የተረጋገጠበት አለማቀፍ ተቋም ይኖር ዘንድ ትጠይቃለች።
አረብ ኤምሬትስ በቀጠናውና አለማቀፋዊ መድረኮች ስሟ ተደጋግሞ ይነሳል፤ ሰላምና ደህንነትን የሚያረጋግጡ እንዲሁም ልማትን የሚያፋጥኑ አለማቀፍ ትብብሮች አጋር ናት።
የሀገሪቱ የብሪክስ አባል መሆንም ይህንኑ ተሳትፎዋን እንደሚያጠናክር ይታመናል።