የዓለም ኢኮኖሚ በ30 ዓመት ታሪክ ዝቅተኛውን እድገት በዚህ ዓመት ያስመዘግባል ተባለ
የዓለም ባንክ የዓለም ኢኮኖሚ በ2024 የ2.4 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ብሏል
የቻይና ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ የጂኦ ፖለቲካ ሽኩቻ እና ጦርነቶች ለኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ዋነኛ ምክንያት እንደሚሆኑ ተገልጿል
የዓለም ኢኮኖሚ በ30 ዓመት ታሪክ ዝቅተኛውን እድገት በዚህ ዓመት ያስመዘግባል ተባለ።
በየጊዜው የዓለማችን ኢኮኖሚ ምን እንደሚመስል በብዙ መመዘኛ መስፈርቶች ትንበያውን የሚያወጣው የዓለም ባንክ የ2024 ትንበያውን ይፋ አድርጓል።
እንደ ባንኩ ትንበያ ከሆነ ይህ ዓመት የ2 ነጥብ 4 በመቶ እድገት በማስመዝገብ በ30 ዓመት ታሪክ ውስጥ የዓለም ኢኮኖሚ ዝቅተኛ እድገት ይመዘገብበታል።
የዓለም ኢኮኖሚ በ2020ዎቹ ውስጥ ጥሩ የሚባልብየነበረ ቢሆንም በዘንድሮው ዓመት ግን ዝቅተኛው እድገት እንደሚመዘገብ ባንኩ አስታውቋል።
የሀያላን ሀገራት ጂኦ ፖለቲካ ፍትጊያ፣ የእስራኤል ሀማስ ጦርነት ፣ የዩክሬን ጦርነት እና ሌሎችም ግጭቶች ለኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሚሆኑ ባንኩ ገልጿል።
በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት ታዳጊ ሀገራት የኢኮኖሚ ጫናቸው ይጨምራል ያለው የዓለም ባንክ በተለይም ብድር መክፈል አለመቻል እና የምግብ ቀውስ ይፈጠርባቸዋልም ብሏል።
የአውሮፓ ሀገራት በአንጻራዊነት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ የተባለ ሲሆን በአማካኝ አውሮፓ የ0 ነጥብ 7 በመቶ እድገት እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
የቻይና ኢኮኖሚ ባሳለፍነው ዓመት ካስመዘገበው የ5 ነጥብ 2 በመቶ በዘንድሮ ዓመት ወደ 4 ነጥብ 5 ዝቅ ይላል ተብሏል።
የቻይና ኢኮኖሚ እድገት በቀጣዮቹ ዓመታት መቀዛቀዝ ያሳያል የተባለ ሲሆን የሸማቾች ፍላጎት መቀዛቀዝ፣ እድሜያቸው የገፉ ዜጎች ቁጥር መብዛት እና የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ተገልጿል።
ሕንድ፣ ኒጀር፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ሊቢያ እና ኮቲዲቯር በ2024 ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ የተባሉ ቀዳሚ አምስት ሀገራት ናቸው።
ኢትዮጵያ በዚሁ ዓመት የ6 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ የዓለም ባንክ ትንበያ ያስረዳል።