ሁለቱ ሀገራት በደህንነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል
የእስራኤል የደህንነት ሚኒስትር ኤሊ ኮሄን ሱዳንን በመጎብኘት የመጀመሪያው የእስራኤል ካቢኔ አባል ሆነዋል፡፡ ከደህንነት ሚኒስቴርና ከብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ከተካተቱ ልዑካን ጋር ነው ሚኒስትሩ በካርቱም ጉብኝት ያደረጉት፡፡
ሚኒስትሩ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋር መወያየታቸውን ጄሩሳሌም ፖስት ዘግቧል፡፡
ኤሊ ኮሄን ጉብኝቱ በሀገራቱ መካከል ትብብርን ለመፍጠርና የቀጣናውን ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር ያሲን ኢብራሂም ጋር የዲፕሎማቲክ ፣ የጸጥታና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ሌሎች ከእስራኤል ጋር ይፋዊ ግንኙነት የሌላቸው የቀጣናው ሀገራትም ፣ የሱዳንን ፈለግ በመከተል ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚመሰርቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ሱዳን የአብርሃም ስምምነት ተብሎ የሚጠራውን ከእስራኤል ጋር ሰላም የማውረድ ስምምነት ከተቀበሉ ሀገራት መካከል የምትጠቀስ ናት፡፡
ቴላቪቭና ካርቱም በደህንነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ማቀዳቸውም በዘገባው የተጠቆመ ሲሆን በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የሚገኙ የአረብና የአፍሪካ ሀገራት ምክር ቤት ውስጥ እስራኤል በምትገባበት ጉዳይ ላይም የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡
ጸረ እስራኤል የሆኑ እና ከሱዳን ወደ እስራኤል ሄደው የተመለሱ ስደተኞች እንዲታሰሩ የሚደነግጉ ሕጎችን ለመሰረዝ በመስራት ላይ መሆናቸውን የሱዳን ባለሥልጣናት ለእስራኤል ልዑክ ተናግረዋል፡፡ በእስራኤል 6ሺ 200 የሱዳን ስደተኞች እንደሚገኙም ተዘገቧል፡፡
እስራኤል ከአረቦች ጋር ባደረገቻቸው ሁለት ጦርነቶች ላይ ሱዳን ወታደሮቿን ልካ መሳተፏን ያስታወሰው ዘገባው፣ እ.ኤ.አ በ1967 ከተካሔደው የ 6 ቀናቱ ጦርነት በኋላ ከእስራኤል ጋር ሰላም ላለመፍጠር ፣ ለእስራኤል እውቅና ላለመስጠት እና ድርድር ላለማድረግ የሚደነግገው ስምምነት የተደረሰበትን የካርቱም ስብሰባ አስተናግዳለች፡፡