የእስራኤል ባለሥልጣናት የሰላም ስምምነቱን ለማጠናቀቅ ወደ ሱዳን ሊያቀኑ ነው
የሁለቱን ሀገራት የሰላም ስምምነት ባበሰሩበት የስልክ ውይይት ነበር ትራምፕ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ያስቆጣ ንግግር ያደረጉት
ምንም እንኳን በሱዳን መሪዎች በኩል መከፋፈል ቢኖርም ሁለቱ ሀገራት የተለያዩ ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል
የእስራኤል ባለሥልጣናት የሰላም ስምምነቱን ለማጠናቀቅ ወደ ሱዳን ሊያቀኑ ነው
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን መደበኛ ለማድረግ የሚያስችላቸውን እርምጃ ለመውሰድ አርብ ዕለት ከተስማሙ በኋላ የእስራኤል ልዑክ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ሱዳን እንደሚጓዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ገለጹ፡፡
ኔታንያሁ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የእስራኤል ልዑካን ስምምነቱን ለማጠናቀቅ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ሱዳን ይሄዳሉ” ብለዋል፡፡
በአሜሪካ አደራዳሪነት የተደረሰው ስምምነት ሱዳንን ባለፉት ሁለት ወራቶች ከእስራኤል ጋር ጠላትነትን ወደ ጎን ያደረገች ሦስተኛዋ የአረብ ሀገር ያደርጋታል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ልዑካን በግብርና ፣ ቴክኖሎጂ ፣ በአቪዬሽን ፣ በስደት ጉዳዮች እና በሌሎችም የትብብር ጉዳዮች ላይ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ እንደሚወያዩም ተገልጿል፡፡
ስምምነቱን ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ግን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ወታደራዊ እና ሲቪል መሪዎች ከእስራኤል ጋር የሚመሰረተው ግንኙነት በምን ያህል ፍጥነት እና እስከ ምን ያህል ርቀት መሄድ እንዳለበት በተመለከተ ስለመከፋፈላቸው ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ሰፋ ያለና መደበኛ ግንኙነትን ለመቀጠል ገና ያልተቋቋመው ፓርላማ ሀሳቡን እንዲያጸድቅ ይፈልጋሉ ፤ ይህ ደግሞ ከጉዳዩ ስሜታዊነት እና ከሲቪሉና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ልዩነቶች አንፃር ሂደቱን ሊያዘገየው እና ሊያወሳስበው እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳንን ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ስፖንሰር አድራጊዎች ዝርዝር ውስጥ ለማስወጣት በዚህ ሳምንት የወሰዱት ውሳኔ ለስምምነቱ መንገድን የከፈተ ሲሆን ፣ ይህም እ.ኤ.አ. ህዳር 3 በሚካሔደው ምርጫ በድጋሚ ለመመረጥ ለሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት አንድ የውጭ ፖሊሲ ስኬት መሆኑን ያሳያል፡፡ ትራምፕ በቅድመ ምርጫ አስተያየቶች ከዴሞክራቲክ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን በጥቂት ልዩነት እየተመሩ እንደሚገኙ ይገለጻል፡፡
ትራምፕ የእስራኤል-ሱዳን ስምምነትን ከእስራኤል ጠ/ሚኒስተር ኔታንያሁ ፣ ከሱዳኑ አቻቸው ሃምዶክ እና የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት ሀላፊ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር ወቅት ነበር ያረጋገጡት፡፡ ከእስራኤል ጋር ግንኙነቶችን መደበኛ ለማድረግ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን መሪነት እንድትከተል የትራምፕ አስተዳደር ሱዳንን ለሳምንታት ሲያግባባ ቆይቷል፡፡
በመሪዎቹ የስልክ ውይይት ወቅት “ ‘እንቅልፋሙ ጆ’ (ባይደን) ይህንን ስምምነት ማድረግ ይችል ነበር ብለው ያስባሉ?” ሲሉ ትራምፕ ለኔታንያሁ መስቀለኛ ጥያቄ አንስተው ነበር
በዋሽንግተን በሁለቱም ወገን በኩል ለእስራኤል ድጋፍ እንዳለ እምነት ያላቸው ኔታንያሁ ጥያቄውን አጣጥለውታል ፡፡
“ደህና ሚስተር ፕሬዚዳንት ልነግርዎት የምችለው አንድ ነገር ነው ... በአሜሪካ ውስጥ ከማንኛውም አካል ለሰላም የሚደረገውን እገዛ እናደንቃለን” ሲሉ መልሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች” የውሃ ፍላጎቷን ስለሚገታ “አንድ ነገር ማድረግ አለባት” በሚል ጸብ አጫሪ እና ግብጽን ለጦርነት የሚያበረታታ የሚመስል ንግግርም ያደረጉት በዚሁ የስልክ ውይይት ላይ ነው፡፡ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በውይይቱ ወቅት የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በሚካሔደው ውይይት እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱን ንግግር በመቃወም የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ ከማውጣትም ባለፈ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ የሚገኙትን የአሜሪካ አምባሳደር በመጥራት በንግግሩ ዙሪያ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የተለያዩ የአሜሪካ ሰሴናተሮችን እና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ በበርካታ አካላትም ተተችቷል፡፡