ፒዮንግያንግ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቀን ተመሳሳይ ሙከራ ልታደርግ እደምትችል ይጠበቃል
ሰሜን ኮሪያ በትላንትናው እለት ለቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መልዕክት ነው ያለችውን የአህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ አደረገች፡፡
“በኪም የመሪነት ዘመን ሰሜን ኮሪያ የሀገሪቱን መከላከያ ሀይል ፍፁም የበላይነትን በማስጠበቅ ትልቅ ደረጃ ያደረሰውን ወሳኝ የሚሳይል ሙከራ ተደርጓል” ሲል የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ኬሲኤንኤ ዘግቧል፡፡
ሁዋሶንግ 19 የተባለው አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል የኒውክሌር አረርን መሸከም የሚችል ሲሆን 7 ሺህ ኪሎሜትር ከፍታ መምዘግዘጉ ነው የተሰማው፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሀገሪቱ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን መሸከም የሚችሉ የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን በማምረት ረገድ የማይቀለበስ ደረጃ ላይ መድረሷን ተናግረዋል።
የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ የዜና አገልግሎት የደቡብ ኮሪያን ጦር ጠቅሶ እንደዘገበው ሚሳይሉ በከፍተኛ ፍጥነት ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ አቅራቢያ ንጋት ጠዋት አንድ ሰአት አካባቢ ነው የተወነጨፈው፡፡
በምስራቅ ባህር ከመውደቁ በፊትም አንድ ሺህ ኪሎሜትሮችን እንደተጓዘ ጦሩ ያሰራጨው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከአንድ አመት በኋላ በአይነቱ የመጀመርያው የሆነው አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ በመጪው ማክሰኞ ከሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የተደረገ ነው።
ተንታኞች እንዳሉት የሰሜን ጠብ አጫሪ ድርጊት ዓላማው የኒውክሌር መሳርያዎችን ወደ አሜሪካ የማድረስ አቅሟን ለማሳየት ነው ።
የደቡብ ኮሪያ የደህንነት ተቋማት የፒዮንግያንግ ሙከራ በዛሬ ብቻ እንደማያበቃ እና ህዳር አምስት ማክሰኞ በ2024 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቀን ተመሳሳይ ሙከራ ልታደርግ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ሁዋሶንግ 19 የተባለው ሚሳይል 1 ሺ አንድ ነጥብ ሁለት ኪሎሜትር በ7687 ከፍታ ለ86 ደቂቃዎች መጓዙ ተዘግቧል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ድርጊቱን አውግዘው የጸጥታው ምክር ቤትን የውሳኔ ሀሳብ የተላለፈ ነው ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ ከምእራቡ አለም እና ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ጋር የተካረረ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው ፒዮንግያንግ ወደ ሩሲያም 10 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን በመላክ እየተወቀሰች ትገኛለች፡፡