“ግድያ እና መፈናቀል ተደጋግፎ እና አብሮ የመኖር ባሕልና ልምድ ካላት አገር ዜጎች የሚጠበቅ አይደለም”- ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ቀኑ የተከበረው ከ2 ዓመት በፊት በአቡዳቢ የተፈረመውን የወንድማማችነት እኅትማማችነት ሰነድ ታሳቢ አድርጎ ነው
ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች የወንድማማችነት እኅትማማችነት ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ተከብሯል
ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች የወንድማማችነት እኅትማማችነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከበረ፡፡
ቀኑ የተከበረው የዓለም ካቶሊካውያን አባት ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቼስኮ እና ታላቁ ኢማም አል አዝሃር አህመድ ኤል ታየብ የተፈራረሙትን የሰው ልጆች የወንድማማችነት እና እኅትማማችነት ለዓለም ሰላምና አብሮ መኖር ሰነድ መሰረት በማድረግ ነው፡፡
ሰነዱ ከ2 ዓመት በፊት በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አቡዳቢ ነበር የተፈረመው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ለሰው ልጆች አብሮነት ለዓለም ሰላምም ይበጃል በሚል ሰነዱ የተፈረመበትን ቀን ጥር 27 የወንድማማችነት እና እኅትማማችነት ቀን ሆኖ በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ወስኗል፡፡
ድርጅቱ ቀኑ እንዲከበር የወሰነው ዩኤኢ፣ ባህሬይን፣ ግብጽ እና ሳዑዲ አረቢያ ባቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ መሰረት ነው፡፡ በመሆኑም እ.ኤ.አ የካቲት 4 በየዓመቱ የሰው ልጆች የወንድማማችነት እኅትማማችነት ቀን ሆኖ ይከበራል፡፡
ኢትዮጵያም ቀኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኘው የድርጅቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የሃይማኖት አባቶች እና ታላላቅ ሰዎች በተገኙበት አክብራለች፡፡
ሃገራችን በታሪኳ የምትታወቀው ባላት የሃይማኖቶች ብዝሃ እና ትብብር ነው ያሉት የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን አባት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የምናየው ብሄርና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ግድያ እና መፈናቀል ተደጋግፎና አብሮ የመኖር ባሕልና ልምድ ካላት አገር ዜጎች የሚጠበቅ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
በሠነዱ ውስጥ ማዕከላዊ መልእክት ሆኖ የምናገኘውን የወንድማማችነት/እኅትማማችነት ፅንሰ ሀሳብ ከምንጊዜውም በላይ መሣርያችን አድርገን በየአካባቢያችን ልንከተለው ይገባልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድረስ በበኩላቸው የቀኑ መከበር አስፈላጊነት አንስተዋል፡፡
ሁሉም ሃይማኖቶች ወንድማማችነትንና እኅትማማችነትን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ያስተምሩ እንደነበር ያስታወሱት ሃጂ ዑመር አሁንም ለተግባራዊነቱ መትጋት ያስፈልጋል በሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሜን ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ከሚገኛው የዩኤኢ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ የአከባበር ስነ ስርዓት እና ዐውደ ጥናት ላይ ምሁራን እና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡