ከ197 በላይ ሀገራት የተሳተፉበት ኮፕ28 አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በተባበሩት አረብ ኢምሬት ዱባይ ተካሂዷል
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በኮፕ28 ጉባኤ ዙሪያ የሰሩት ዘገባ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ያዘጋጃል።
የዘንድሮው ኮፕ28 ጉባኤም በተባበሩት አረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት የተካሄደ ሲሆን ባሳለፍነው እሮብ ጉባኤው ፍጻሜውን አግኝቷል።
በዱባይ ለ12 ቀናት የተካሄደውን ይህን ጉባኤ በርካታ የዓለማችን ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል።
ሰፊ ሽፋን ከሰጡ ዓለም አቀፍ ብዙሀን መገናኛዎች መካከል ሮይተርስ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ብሉምበርግ፣ ቢቢሲ፣ ዘ ኢንዲፐንደንት፣ ዘ ኢኮኖሚስት፣ ሲኤንኤን፣ ኒዮርክታየምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ታየም፣ ሎስአንጀለስ ታየምስ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ዓለም ቀቀፍ ሚዲያዎች የኮፕ28 ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የአረብ ኢምሬት ኢንዱስትሪ ሚንስትር ዶክተር ሱልጣን አልጃቢር ላሳዩት አመራር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኢምሬት ጉባኤውን ያስተናገደችበት መንገድ፣ መስተንግዶ እና አጠቃላይ ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ማድረጓንም እነዚህ ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ሚዲያዎቹ በዘገባዎቻቸው ላይ ስለ ጉባኤው አስፈላጊነት፣ ስለ አረብ ኢምሬት ስምምነት፣ በጉባኤው ላይ ስለተላለፉ ሌሎች ስምምነቶች እና ሀገሪቱ ስላበረከተችው አስተዋጽኦም እነዚህ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል።
በጉባኤው የተሳተፉ ከ200 በላይ ሀገራት ስለ አየር ንብረት ለውጥ ፣ እያደረሰው ስላለው ጉዳት እና ከጉዳቶች ማገገም ስለሚችሉበት ሁኔታ በስፋት ተወያይተው ከመፍትሄ ላይ የደረሱበት እንደነበርም ተገልጿል።
ሀገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ለመቀነስ በሚል ቀስ በቀስ ነዳጅን እንደ ሀይል አማራጭነት ከመጠቀም እንዲታቀቡም ተስማምተዋል ሲሉ ሚዲያዎች ትኩረት ሰጥተው ዘግበዋል።
የጉባኤው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አልጃቢር ለምድራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ያሳዩት የዲፕሎማሲ ጥረትም የሚደነቅ መሆኑ ተዘግቧል።