የሚወሰልቱ ሰዎችን የሚያድነው የሴቶች የስለላ ቡድን - “ፎኒክስ ስኳድ”
“የታማኝነት ዘብ” ነን የሚለው ቡድኑ ከድብቅ ካሜራዎች እስከ ድሮኖች በመጠቀም በስአታት ውስጥ ወሳኝ መረጃዎችን ይሰበስባል
ቡድኑ በ20 አመታት ልምዱ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ የታማኝነት ጥያቄ እንደሚነሳባቸው ማረጋገጡን ይገልጻል
በፔሩ የሚወሰልቱ ሰዎችን አድኖ የሚይዘውና በሴቶች ብቻ የተዋቀረው ቡድን የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ስቧል።
ራሳቸውን “ፎኒክስ ስኳድ” ብለው የሚጠሩት የቡድኑ አባላት ከደንበኞቻቸው የሚቀርብላቸውን ጥያቄ ተቀብለው በስአታት ውስጥ ወሳኝ መረጃን የማቅረብ ክህሎት አላቸው ተብሏል።
“ፎኒክስ ስኳድ” በደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በተለያዩ መሳሪያዎችና ብልሃት የተሞላባቸው ዘዴዎች ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠቱን ጀሲካ ሜሊና የተባለችው የቡድኑ መሪ ትናገራለች።
የትዳር አጋራቸው ታማኝነት የሚከነክናቸው የፔሩ ነዋሪዎች ወደነጀሲካ ቢሮ በመምጣት አጣሩልኝ ብሎ በጠየቀ በስአታት ውስጥ ምላሽ እንደሚያገኙም ነው የተገለጸው።
የቡድኑ አባላት ድብቅ ካሜራዎችን እና የቆዩ የስለላ ስራ ጥበቦችን ይጠቀማሉ፤ ጉዳዩ ከባድ ያለ ከመሰላቸውም ድሮን እስከመጠቀም ይደርሳሉ።
“ፎኒክስ ስኳድ” የውስልትና አጣሩልኝ ጥያቄ የሚያቀርቡ ወንዶችንም ሆነ ሴቶች ያለአድልኦ የሚያስተናግዱ ቢሆንም ሁሉም አባላቱ ሴቶች ናቸው።
“የራሴን የስለላ ቡድን ሳቋቁም ሴቶችን ብቻ በአባልነት ለማካተት የወሰንኩት ሴቶች የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ስላመንኩ ነው” ትላለች መስራቿ ጀሲካ ሜሊና ከላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቆይታ።
ሴቶች ምንም ሳይታወቅባቸው፤ ገጽታቸውን በፍጥነት ቀያይረው ውስብስብ የሚመስልን ነገር በፍጥነት መፍታት እንደሚችሉም በማከል።
“ፎኒክስ ስኳድ” የተቋቋመው ፍቺ እየፈለጉ ለፍርድ ቤት የሚያቀርቡት ታማኝነት ያለው ማስረጃ ያጡ ሰዎችን ችግር ለመፍታት ነው።
አዳ ሂኖስትሮቫ የተባለች የቡድኑ አባልም “የሚመጡልን ጉዳዮች የተለያዩ ቢሆኑም ቡድናችን በስአታት ውስጥ ለባለጉዳያችን የሚፈልገውን ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን” ትላለች።
በአራት ስአት ውስጥ ያጠናቀቁት ተልዕኮም ፈጣኑ ሆኖ መመዝገቡን ታወሳለች።
የ“ፎኒክስ ስኳድ” አባላት ራሳቸውን “የታማኝነት ዘብ” አድርገው ነው የሚመለከቱት፤ በትዳር አጋራቸው እና ፍቅረኛቸው ላይ የሚወሰልቱ ሰዎችን በአይነ ቁራኛ የሚጠብቁና ሲጠየቁም መረጃ የሚያቀብሉ።
ሴቶችን ብቻ በአባልነት የያዘው የስለላ ቡድን የ20 አመት ግኝት አስገራሚ ነው፤ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ የታማኝነት ችግር ይታይባቸዋል ይላል።
ሊዝ ሮድሪጌዝ የተባለች የቡድኑ አባል እንደምትለው በሁለት አስርት አመታት ከመረመሯቸው የውስልትና ጉዳዮች 70 በመቶው ታማኝነት የራቃቸው ሴቶችን የተመለከቱ ናቸው።
የቡድኑ መስራች ጀሲካ ሜሊናም በየሳምንቱ ከምትመረምራቸው 10 ጉዳዮች ስምንቱ ለትዳር አጋራቸው ታማኝ ያልሆኑ ሴቶችን የተመለከቱ መሆናቸውን ገልጻለች።
የሴቶች ታማኝነት በብዛት ጥያቄ ውስጥ የገባው ምናልባትም ሴቶች የትዳር አጋራቸውን ታማኝነት በ“ፎኒክስ ስኳድ” ማሰለል ሳይፈልጉ ወይም መረጃው ሳይኖራቸው ቀርቶ ሊሆን ይችላል።