ተሸከርካሪው ከአውቶብስነት ወደ ባቡርነት ለመቀየር 15 ሰከንድ ብቻ ይፈጅበታል
ጃፓን ከሰሞኑ በአስፓልት መንገድ ላይ እና በባቡር ሀዲድ ላይ የሚንቀሳቀስ አዲሱ ሁለገብ ተሸከርከሪ ይፋ አድርጋለች።
አዲሱ የጃፓን ተሸከርካሪ አስፓልት ላይ ሲሆን በተገጠመለት ጎማ እንደ አውቶብስ የሚጓዝ ሲሆን፤ በባቡር ሀዲድ ላይ ሲሆንም እንደ ባቡረ የሚያገለግል ነው ተብሏል።
አዲሱ የባቡር እና የአውቶብስ ቅይጥ ተሸከርካሪው በጃፓና ካኢዮ ከተማ ለህዝብ ይፋ መደረጉንም ኦዲቲ ሴንተራል በድረ ገጹ አስነብቧል።
የመለስተኛ አውቶብስ ቅርጽ እና በመጠን ያለው ተሸከርካሪው በመልኩ የሰው አይን ውስጥ መግባት ባይችልም፤ በሚሰጠው አገልግሎት ግን የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።
ተሸከርካሪው በአስፓልት ላይ ሲሆን በመደበኛ ጎማ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ በሀዲድ ላይ ሲወጣ ደግሞ ልክ እንደ ባቡር ሁሉ በተገጠመለት የብረት ጎማ ሀዲዱ ላይ ይጓዛል ተብሏል።
ተሸከርካሪው ከመለስተኛ አውቶብስነት ወደ ባቡርንት እንዲሁም በተቃራኒው ከባቡርነት ወደ አውቶብስነት ለመቀየር 15 ሰከንድ ብቻ እንደሚፈጅም የተሸከርካሪው አምራች ኩባንያ አስታውቋል።
አዲሱ ተሸከርካሪ የህዝብ ትራንስፖርትን ከማዳረስ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው የተባለ ሲሆን፤ በተጨማሪም የቱሪስት መስህብ እንደሚሆን ተነግሯል።
በናፍታ የሚንቀሳቀሰው ተሸከርካሪው 21 ሰዎችን የመጫን አቅም ያለው ሲሆን፤ እንደ ባቡር በመሆን በሰዓት 60 ኪሎ ሜትር እንደ አውቶብስ በመሆን ደግሞ በሰዓት እስከ 100 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል።