በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አጋማሽ የተሰራ ቤተ ክርስቲያን በቁፋሮ ተገኘ
የቅርስ ባለሙያ የሆኑት አቶ ግርማቸው ሙሉጌታ ተጨማሪ የቁፋሮ ስራው በአርኪኦሎጅስቶች ቢቆፈር ለቅርሱ ይዘት ጠቃሚ ነው ብለዋል
በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አጋማሽ የተሰራ ቤተክርስቲያን በቁፋሮ ተገኘ
በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አጋማሽ የተሰራ ቤተክርስቲያን በቁፋሮ ተገኘ
በአማራ ክልል፣በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከ1524 ዓ.ም በፊት ተሰርቶ ጥቅም ይሰጥ የነበረ ጉረባ ጊዎርጊስ ቤተ ክርስቲያን በቁፋሮ መገኘቱን የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በዛሬው እለት አስታውል፡፡
ቅርሱ የተገኘው የሃይማኖት አባቶች ነሃሴ 2 ቀን 2011 ዓ.ም በለንባ ቀበሌ፣ጎርባ ጊዮርጊስ ከመሬት ጋር ተመሳስሎና ተቀብሮ የሚገኝ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አለ ብለው ለአካባቢው አርሷደሮች መንገራቸውን ተከትሎ በተደረገ ቁፋሮ መሆኑንም ነው የአካባቢው ዋሪዎች ያስታወቁት፡፡
በዚህም መሰረት የቅርሱ ቁፋሮ ህዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም መጀመሩን ገልጸዋል። በቁፋሮ በተገኘው ቅርስ የጊዮርጊስ ታቦት፣ ጽንሃ፣ ጸናጽል፣ ዝብድ ወይም የሰም ማቅለጫ፣ጽዋ፣በእሳት የወደሙ ንዋዬ ቅድሳት፣ አጽምና ሌሎችም አንደሚኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ ቁፋሮ ገና ባለመጠናቀቁ ፣ ተጨማሪ ቅርሶች ይገኙበታል ተብሎ የሚታሰበው ቦታ ቁፋሮም ተጀምሮ በመቆሙ ገና ሌሎች ቅርሶች ይገኛሉ የሚል ግምት እንዳለ ነው የተገለጸው፡፡
ከ460 ዓመታት በላይ በከርሰ-ምድር ተቀብሮ የቆየው ቤተ ክርስቲያኑ ከ1529 እስከ 1543 ዓ.ም በተካሄደው የኢማም አህመድ ኢብን አልጋዚ (ግራኝ አህመድ) ጦርነት ተብሎ በሚታወቀው ጊዜ በቃጠሎ እንደወደመ ተነግሯል።
አጠቃላይ ስለቅርሱ አርኪኦሎጂስቶች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣የቅርስ ባለሙያዎች ሙያዊ ጥናት እንዲያደርጉበት ጥሪ መቅረቡንም የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
ህዳር አጋማሽ ላይ ቁፋሮው ተጀምሮ ለተገኘው ቅርስ እስከ አሁን ከአካባቢው አርሶ አደሮች ውጭ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች እንዲሁም የሃገረ ስብከት ተወካዮች እንዳላዩትና አስተያየት እንዳልሰጡበት አርሶ አደሮቹ ገለጸዋል፡፡
ለዘመናት ቅርሱ በከርሰ-ምድር ተቀብሮ የቆየበት የመሬት ባለቤት የሆኑት አርሶ አደር ሞላ አዱኛ 1974 ዓ.ም በምሪት ተቀብለው ማሳውን እያረሱ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ የቅርስ ባለሙያ አቶ ግርማቸው ሙሉጌታ በአርሶ አደሮች ቁፋሮ የተገኘውን ቅርስ ቁፋሮው ስላላቀ፣ከዚህ በኋላ ያለው ቁፋሮ በአርኪኦሎጅስቶች ቢቆፈር ለቅርሱ ይዘት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ውበት መስፍን በበኩላቸው አዲስ ለተገኘው ቅርስ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ይሁንና የቅርሱ ቁፋሮ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት እንክብካቤ እንዳልተደረገለት ወረዳው ገልጿል፡፡