አረብ ኢምሬትስና አሜሪካ በኋይትሀውስ በኃይል ኢንቨስትመንት ጉዳይ ውይይት አካሄዱ
አረብ ኢምሬትስ ከ2018-2023 በአሜሪካ ያደረገችው ኢንቨስትመንት 3.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል

የሁለቱ ሀገራት ነዳጅ ያልሆነ የንግድ ልውውጣቸው 40 ቢሊዮን ገደማ የደረሰ ሲሆን የሸቀጦች ንግድ በ2024 34.43 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል
አረብ ኢምሬትስና አሜሪካ በኋይትሀውስ በኃይል ኢንቨስትመንት ጉዳይ ውይይት አካሄዱ።
በአሜሪካ የአረብ ኢምሬትስ አምባሳደር ዮሱፍ አል ቃታይባ እና የአረብ ኢምሬትስ የኢንዱስትሪና የአድቫንስድ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃብር ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ዲጄ ቫንስ ጋር በኃይትሀውስ ተገናኝተዋል።
አረብ ኢምሬትስና አሜሪካ በኃይል ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ አመራር እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።
አረብ ኢምሬትስ በመካከለኛው ምስራቅ ብሎም በዓለም የአሜሪካ ወሳኝ አጋር ስትሆን ሁለቱ ሀገራት ትብብራቸውን በማጠናከር ለቀጣናውና ለአለም ደህንነት እንዲሁም ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሀገራቱ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በጠፈር ምርምር እና በሌሎች ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ለሚያደርጉት ትብብር ጥሩ መሰረት ጥለዋል።
የሁለቱ ሀገራት ነዳጅ ያልሆነ የንግድ ልውውጣቸው 40 ቢሊዮን ገደማ የደረሰ ሲሆን የሸቀጦች ንግድ ደግሞ በ9.47 በመቶ አድጎ በ2024 34.43 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ይህ በ2023 ከነበረው 31.45 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ አሳይቷል።
አረብ ኢምሬትስ ከ2018-2023 በአሜሪካ ያደረገችው ኢንቨስትመንት 3.7 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን አሜሪካ በተመሳሳይ ወቅት በአረብ ኢምሬትስ 9.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጋለች።
ሀገራቱ አንዳቸው በሌላኛቸው ሀገር የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት እያጠናከሩ ሲሆን አረብ ኢምሬትስ በአሜሪካ ኢነርጂ ዘርፍ 70 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጋለች።