አረብ ኢምሬትስ አሜሪካ ውስጥ ኢንቨስት ያደረገችው ከ35 ቢሊዮን ዶላር አለፈ
የአረብ ኢምሬትስ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሼክ ታህኑን ቢን ዛይድ አልናህያን በአሜሪካ የማያደርጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በዛሬው እለት ጀምረዋል

ሼክ ታህኑን ቢን ዛይድ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ትብብር ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል
አረብ ኢምሬትስ አሜሪካ ውስጥ ኢንቨስት ያደረገችው ከ 35 ቢሊዮን ዶላር አለፈ።
ምክትል የዱባይ ገዥና የአረብ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሼክ ታህኑን ቢን ዛይድ አልናህያን በአሜሪካ የማያደርጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በዛሬው እለት ጀምረዋል።
ሼክ ታህኑን ቢን ዛይድ በኃይትሀውስ ከበርካታ የአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በሁለት ሀገራት መካከል በሚደረግ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ትብብር ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ውይይት እንደሚያደርጉ የኢምሬትስ ዜና አገልግሎት ዋም ዘግቧል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆነችው ሁዳ አል ማላህ የሼክ ታህኑን ቢን ዛይድ የአሜሪካ ጉብኝት አስርት አመታትን ላስቆጠረው ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጠንካራ አንደምታ አለው ብላለች።
ባለሙያዋ ለአል ዐይን ኒውስ እንደተናገረችው አረብ ኢምሬትስ በአሜሪካ በተለያዩ ዘርፎቾ ላይ ኢንቨስት ካደረጉ ሀገራት ቀዳሚ ነች።
የአሜሪካ-አረብ ኢምሬትስ ንግድ ልውውጥ
በአሜሪካና በአረብ ኢምሬትስ መካከል በኃይል፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ያለው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በርካታ አስርት አመታትን ያስቆጠረ ነው።
አረብ ኢምሬትስ አሜሪካ ውስጥ በቴክኖሎጂ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በመሰረተልማት እና አምራች ኢንዱሰትሪዎች ዘርፎች ከ35 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ የአሜሪካ ኢኮኖሚን ለመደገፍ እና አለምአቀፍ ተደራሽነቷን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች። አሜሪካ በአንጻሩ ከ2018-2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በአረብ ኢምሬትስ ውስጥ ኢንቨስት ያደረገችው 9.4 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ነዳጅ ያልሆነው(non-oil) የንግድ ልውውጥ በ2022 ከነበረበት 23.8 ቢሊዮን ዶላር በ2023 በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ 39.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
በ2024 የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት በመካከላቸው የነበረው ነዳጅ ያልሆነው የንግድ ልውውጥ 28.3 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን በ2019 ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ46.2 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።
አል ማላህ እንዳለችው ከሆነ የጉብኝቱ ዋና አላማ ኢንቨስትመንት ማስፋፋትና ስትራቴጂካዊ ግንኙነትን ማጠናከር ነው።
አማካሪው ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በሚገናኙበት ወቅት ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ባለፈ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ባሉ ወቅታዊ ችግሮች ዙሪያም እንደሚወያዩ ዋም በዘገባው ጠቅሷል።
አረብ ኢምሬትስ በ2023 በውጭ ኢንቨስት ያደረገችው 22.3 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም በአለምአቀፍ ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና ከሚጫወቱት አንዷ እንድትሆን አስችሏታል።