ፍልስጤማውያን አትሌቶች በፓሪሱ ኦሎምፒክ እንዲሳተፉ ይጋበዛሉ - አለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ
በጦርነቱ ምክንያት በኦሎምፒክ ውድድሩ መሳተፍ የሚያስችል ውጤት ያስመዘገበ ፍልስጤማዊ አትሌት የለም
አለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በሩሲያ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ በእስራኤል ላይ አለመድገሙ ቅሬታ አስነስቶበታል
ፍልስጤማውያን አትሌቶች በፓሪሱ ኦሎምፒክ እንዲሳተፉ ይጋበዛሉ አለ አለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ።
ሰባት ወራት ሊደፍን በተቃረበው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ምክንያት በሀምሌ ወር በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር መሳተፍ የሚያስችል ውጤት ያስመዘገበ ፍልስጤማዊ አትሌት የለም።
ይሁን እንጂ አለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ከስድስት እስከ ስምንት ፍልስጤማውያን አትሌቶች እንዲሳተፉ እንደሚጋብዝ ነው የኮሚቴው ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመለየት የሚካሄዱ ውድድሮች መቀጠላቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፥ ኮሚቴው ፍልስጤማውያን አትሌቶች ልምምዳቸውን እንዲቀጥሉና በሚኒማ ማሟያ ውድድሮች እንዲሳተፉ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።
የአለም ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው ሩሲያ ላይ የወሰደውን እርምጃ ግን በጋዛ ከ34 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ህይወት የቀጠፉ እርምጃዎችን በወሰደችው እስራኤል ላይ ተግባራዊ አላደረገም።
የሩሲያ አትሌቶች በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ በግላቸው እንጂ ሀገራቸውን ወክለው እንዳይወዳደሩ መታገዳቸው ይታወሳል።
የሩሲያ አትሌቶች በፓሪሱ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ የዩክሬኑን ጦርነት በይፋ አለመደገፍና በሩሲያ መከላከያ እና ደህንነት ተቋማት አለመስራታቸው መረጋገጥ አለበት ተብሏል።
የአለም ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሞስኮ ላይ ማዕቀብ የጣለው ዩክሬንን በመውረር የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አውድማለች በሚል ነው።
ኮሚቴው በጋዛ ከባድ ጥፋት እያደረሰች ባለችው እስራኤል ለምን ተመሳሳይ እርምጃ አልወሰደም የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ቶማስ ባች፥ “በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ያለው ጦርነት ከሩሲያና ዩክሬን በፍጹም የተለየ ነው” ብለዋል።
ሃማስ በጥቅምት 7 2023 የፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ያደረሰውን ጉዳት “አሰቃቂ” ብለው የገለጹትባች፥ ጋዛን እያፈራረሰች ለምትገኘው እስራኤል ለመከላከል ሞክረዋል።