የጸጥታ ሀይሎች ሁሉንም ስደተኞች በመሰብሰብ “የመጨረሻ ጸሎታችሁን አድርጉ አሉን”
ስደተኞቹ በእስር ቤቱ ያለውን አያያዝ እንዲያስተካክል ተቃውሞ እያሰሙ ነበር
በየመን እስር ቤት በረሃብ አድማ ላይ በነበሩ ስደተኞች ላይ ሀውቲዎች በተኮሱት ከባድ መሳሪያ እሳት መነሳቱን ሂዩማን ራይትስ ዋች ገለጸ
ባሳለፍነው ሳምንት በየመን ሰነዓ በሚገኝ የስደተኞች እስር ቤት በተነሳው እሳት በርካታ ስደተኞች ህይወት ማለፉ ያታወሳል፡፡
የእሳት አደጋውም የሀውቲ የጸጥታ ሀይሎች በስደተኞች እስር ቤት ላይ ለጊዜው ምንነቱ ያልታወቀ ከባድ መሳሪያ በመተኮሳቸው የደረሰ መሆኑን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ የመብት ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ያስታወቀው የመብት ድርጅቱ፤ ስደተኞቹ በእስር ቤቱ ያለውን አያያዝ እንዲያስተካክል ተቃውሞዋቸውን እያሰሙ ነበር ተብሏል።
በጥቃቱም የበርካቶች ህይወት ማለፉ የተገለጸ ሲሆን፥ ከአዳጋው የተረፉ በርካታ ስደተኞችም ህክምና እያገኙ መሆኑን ገልጿል።
በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ቁጥጥር በመኖሩ የተራድኦ ድርጅቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ስደተኞች ለመድረስ እንዳልቻሉም ተነግሯል።
አንሳር አላህ በመባል የሚታወቀው የሀውቲ ታጣቂ ቡድን የተራድኦ ድርጅቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የህክምና እና ሌሎች ድጋፎችን እንዲያደርሱ እንዲፈቅድም ጠይቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በየመን ሰነዓ እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ እንዲያጤው እና በሀገሪቱ የሚካሄዱ የሰበአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምርም ጥሪ አቅርቧል።
እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) መረጃ መሰረት ከ6000 በላይ ስደተኞች በየመን እስር ቤቶች ውስጥ በእስር ላይ ይገኛሉ።
ሂዩማን ራይትስ ዋች በእስር ላይ የሚገኙ 5 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጋር ያደረገው ቆይታ…
ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ስደተኞች እስር ቤቶቹ ከፍተኛ ንጽህና ጉድለት እንዳለበት እና እስከ 550 የሚደርስ ስደተኞች በረሃብ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
የሚተኙበት ፍራሽ ከእስር ቤቱ እንደማይቀርብላቸው የሚናገሩት ስደተኞቹ፥ ፍራሽ ካስፈለጋቸው ከእስር ቤቶች ጠባቂዎች በገንዘብ እንደሚገዙ፤ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እና መጠጥ ውሃ ችግር እንዳለም ተናግረዋል።
ከእስር ቤቶቹ ብቸኛ መውጫ መንገድም ለጠባቂዎች እስከ 70 ሺህ የየመን ሪያል (280 የአሜሪካ ዶላር) መክፈል እንደሆነም ይናገራሉ።
በተጨናነቀ እስር ቤቶች ውስጥ የቆዩት እስረኞቹ በእስር ቤቶቹ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በመቃወም የረሃብ እድማ ጠርተው እንደነበረም ስደተኞቹ ገልጸዋል።
ባሳለፍነው የካቲት 28 እስረኞቹ ቁርስ እና ምሳ ቢቀርብላቸውም እምቢ ማለታቸውን በማስታወስ፤ የእስር ቤቱ ጠባቂዎችም የአድማውን አስተባባሪዎች ለይተው በማውጣት ከፍተኛ ድበደባ ፈጽመውባቸዋል ብለዋል።
በዚህ የተናደዱ ስደተኞችም ሰሃን ጨምሮ በእጃቸው የያዙትን በመወርወር ተቃዎዋቸውን መግለጻቸውን እና እስር ቤቱ ጠባቂዎችም ለቀው ከወጡ ከደቂቃዎች በኋላ ተጨማሪ ለየት ያለ ደንብ ልብስ የለበሱና ከባድ መሳሪያ የታጠቁ የሀውቲ ታጣቂዎችን ይዘው መመለሳቸውንም ያስታውሳሉ።
ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ስደተኞች እንደሚናገሩት፥ የጸጥታ ሀይሎች ሁሉንም ስደተኞች በመሰብሰብ “የመጨረሻ ጸሎታችሁን አድርጉ አሉን” ይላሉ።
አዲስ ከገቡ የጸጥታ ሀይሎች ውስጥ አንዱ ከፍ ያለ ቦታ ላይ በመውጣት ሁለት ከባባድ መሳሪያዎችን በማከታተል ወደ እነሱ እንደተኮሰም ይናገራሉ።
የመጀመሪው ከፍተኛ ጭስ የነበረው እና ጭሱም አይናቸውን እንዳቃጠለውና ለመተንፈስ እንዳስቸገራቸው የተናገሩ ሲሆን፥ ቦምብ ነው ብለው የጠሩት ሁለተኛው ግን ከፍተኛ የፍንደታ ድምጽ እንደነበረውና እሳት ማስነሳቱን ተናግረዋል።
በግምት ከ15 ደቂቃ በኋላም ከውጭ የነበሩ ሰዎች ወደ እስር ቤቱ ሰብረው በመግበታት የተረፉትን ወደ ሆስፒታል ማስገባታቸውን ይናገራሉ።
ከእሳት አደጋው በኋላም በርከት ያሉ የሀውቲ ታጣቂዎች ወደ እስር ቤቱ በመግበት ከፍተኛ ጉዳት ያልደረሰባቸውን ማሰር እንደጀመሩም ያስታውሳሉ።