አህመዲነጃድ በኢራን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ ተመዝግበዋል
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሰኔ ወር በሚካሄደው ምርጫ እንዳይሳተፉ 12 አባላት ያሉት ጋርዲያን ካውንስል ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል ተብሏል
ማህሙድ አህመዲነጃድ ኢራንን ከ2005 እስከ 2013 በፕሬዝዳንትነት መምራታቸው ይታወሳል
የኢራን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ በሰኔ ወር መጨረሻ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመፎካከር መመዝገባቸው ተነገረ።
አህመዲነጃድ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ሰኔ 28 2024 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመፎካከር መመዝገባቸውን የሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ይሁን እንጂ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በኢራን ጉዳይ ትልቅ ስልጣን በጨበጠውና 12 አባላት ባሉት ጋርዲያን ካውንስል ከእጩነት ሊሰረዙ እንደሚችሉ ነው የተነገረው።
የሰኔ 28ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪዎች ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ይፋ እንደሚደረጉ ተገልጿል።
የቀድሞው የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባሉ አህመዲነጃድ በፈረንጆቹ 2005 የኢራን ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
በ2009ም ዳግም ተመርጠው እስከ 2013 ስልጣን ላይ የቆዩ ሲሆን ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ መምራት በሚገድበው ህግ ምክንያት ዳግም ሳይወዳደሩ ቀርተዋል።
አህመዲነጃድ በ2009 ዳግም መመረጣቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት እንዲያልፍና በሺዎች ለእስር እንዲዳረጉ ምክንያት የሆነው “አረንጓዴ አመጽ” ሲቀሰቀስ የሃይማኖታዊ መሪው አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ድጋፍ አልተለያቸውም ነበር።
በ2017ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ሲሞክሩ በጋርዲያን ካውንስሉ እጩነታቸው መሰረዙን ተከትሎ ግን የአህመዲነጃድና ሃሚኒ ግንኙነት መሻከሩን ሬውተርስ አስታውሷል።
አህመዲነጃድ በ2018 በቀጥታ ለሃሚኒ በጻፉት ደብዳቤ “ነጻ ምርጫ” እንዲደረግ መጠየቃቸውን ያወሳው ዘገባው፥ በሰኔ 28ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የመሳተፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ይላል።
“ኢራን ከፈለገች የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ ባለቤት ትሆናለች” በሚለውና ሌሎች አወዛጋቢ ንግግሮቻቸው የሚታወሱት የ67 አመቱ ማህሙድ አህመዲነጃድ፥ በኢራን መንግስት ባለስልጣናት የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥና ለአለም መሪዎች መልዕክቶችን በመጻፍ ይታወቃሉ።
በፈረንጆቹ 2008 ሀገራቸው የኒዩክሌር ኃይል ግብዓት የሆነውን የዩራኒየም ምርቷን መጨመሯን በማስታወቅም ስጋት መፍጠራቸው አይዘነጋም።
በአይሁዳውያን የዘር ፍጅት (ሆሎኮስት) ዙሪያ አወዛጋቢ ጥያቄ የሚያነሱት አህመዲነጃድ በእስራኤልና ምዕራባውያን ዘንድ የሚወደዱ ባይሆኑም በድሃ ተኮር ስራቸው ግን በሀገራቸው ዜጎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ፕሬዝዳንት እንደነበሩ ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሰኔ 28ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ ከተፈቀደላቸው ዋነኛ የቅስቀሳቸው ነጥብ በምዕራባውያን ማዕቀብ የተዳከመውን የቴህራን ኢኮኖሚ ማንሰራራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሏል።