አንሶላ እና የትራስ ልብስ በምን ያህል ጊዜ ልዩነት መቀየር ይኖርበታል?
በአልጋ ልብሶች ላይ የሚያድጉ ባክቴሪያ እና ፈንገሶች የቆዳ ሽታ ፣ አስም እና ስር የሰደደ የሳምባ ኢፌክሽን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
የሰው ልጅ በአማካኝ የቀኑን አንድ ሶስተኛ አልጋ ላይ ያሳልፋል
ከረጅም ቀን በኋላ ሞቃታማ አልጋ ውስጥ እንደመተኛት እና ጭንቅላትንም ለስላሳ ትራስ ላይ ማሳረፈን የመሰለ ነገር የለም፡፡
ነገር ግን የአልጋ ልብስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች፣ ፈንገሶች እንዲሁም ቫይረሶች መገኛ እና መፈልፈያ መሆኑን የምናውቀው ስንቶቻችን ነን?
እነዚህ ባክቴሪያዎች መራባት የሚችሉበት ሞቅ ያለ ቦታ፣ ላብ፣ የሞቱ የቆዳ ህዋሶችን ከአንሶላ እና ትራስ ላይ ማግኝት ይችላሉ፡፡
ሳይንስ እንደሚነግረው የሰው ልጅ በቀን 500 ሚሊየን የቆዳ ህዋሶችን ያስወግዳል፡፡ ታድያ ለረጅም ጊዜ ሳይቀየር ወይም ሳይታጠብ በሚሰነብት የአልጋ ልብስ ላይ እነዚህን ሴሎች እየተመገቡ የሚያድጉ ባክቴሪያ እና ቫይረሶች ከባድ ኢንፌክሽኖችን ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው፡፡
በ2013 አሜሪካን ስሊፕ የተባለ የአልጋ አምራች ኩባንያ ለሳምንት ካልታጠበ የትራስ ልብስ ላይ በእያንዳንዱ ስኩየር ኢንች ላይ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ባክቴሪያዎችን መገኝታቸውን አስታውቆ ነበር፡፡
ይህም በመጸዳጃ ቤት መቀመጫ ላይ ከሚገኘው በ17 ሺህ እጥፍ እንደሚበልጥ ነው የተነገረው፡፡
ከዚህ ባለፈም ለአመታት ሳይቀየሩ አገልግሎት በሚሰጡ ትራሶች ላይ በቢሊየን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች እንደሚገኙ የሚነግረው የተለያዩ የጥናት ውጤቶችን የዳሰሰው የቢቢሲ ዘገባ፤ በመኝታ ወቅት የሚፈጠረው ሙቀት በትራስ ላይ ከሚከማቸው አቧራ እና ሌሎችም ጥቃቅን ህዋሳት ጋር ሲደመር ለባክቴሪያዎች እድገት ምቹ እንደሚያደርገው አመላክቷል፡፡
በርካታ ሰዎች በተለምዶ የትራስ እና የአልጋ ልብሳቸውን የሚቀይሩት አልፎ አልፎ በመሆኑ አንሶላው ከታጠበ በኋላም እንኳን ፈንገሶች ያለምንም ችግር ለአመታት የመቆየት አቅም እንዲኖራቸው አድርጓል ነው የተባለው፡፡
በጊዜ ሂደት እየጠነከሩ የሚመጡት ፈንገስ እና ባክቴሪያዎች አላርጂክ ፣ የቆዳ በሽታ ፣ አስም ፣ በሽታ የመከላከል አቅምን ማዳከም እና ስር የሰደደ የሳምባ ኢንፌክሽንን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ሉኪሚያ ፣ የአካል ክፍሎች ንቅለ ተከላ ያደረጉ እና በሰውነታቸው ላይ ቁስል ያለባቸው ሰዎች ቶሎ ቶሎ በሚቀየር አንሶላ እና ትራስ ላይ ካልተኙ የጤና ሁኔታቸውን ይበልጥ ሊያባብሰው ይችላል፡፡
በመሆኑም ትራሶች ቢበዛ በየሁለት አመቱ እንዲቀየሩ አንሶላ እና የትራስ ልብሶች ደግሞ በየሳምንቱ በመቀየር የቆሸሹትን አንሶላዎች በሞቀ ወሀ ማጠብ ከዛም መተኮስ የባክቴሪያዎችን የመራባት እድል ይቀንሰዋል ተብሏል፡፡