እስራኤል ከየመን የተወነጨፈ ሚሳይል አከሸፍኩ አለች
የየመን ሀውቲ ታጣዎች ለሀማስ አጋርነታቸውን ለማሳየት በእስራኤል ላይ የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ
የእስራል ጦር ከገጸ ምድር ወደ ገጸ ምድር የተወነጨፈውን ሚሳይል 'አሮው' በተባለው የመከላከያ ስርዓት ከእስራኤል ውጭ ከሽፏል" ብሏል
የእስራኤል ጦር ዛሬ ጨዋት ከየመን የተወነጨፈ ሚሳይል ማክሸፉን አስታውቋል።
"በማዕከላዊ እስራኤል የማስጠንቀቂያ ደዎል ከተሰማ በኋላ ከየመን የተወነጨፈው ከገጸ ምድር ወደ ገጸ ምድር የሚወነጨፈው ሚሳይል 'አሮው' በተባለው የመከላከያ ስርዓት ከእስራኤል ውጭ ከሽፏል" ብሏል ጦሩ ባወጣው መግለጫ።
ጦሩ አክሎም በአሁኑ ወቅት የእስራኤልን ጦር የመከላከያ መመሪያዎች መቀየር አያስፈልግም ብሏል። የየመን ሀውቲ ታጣዎች የእስራኤል- ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ለሀማስ አጋርነታቸውን ለማሳየት በእስራኤል ላይ የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ።
ሀውቲዎች ባለፈው ሐምሌ ወር በቴልአቪቭ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈጸሙት የሚሳይል ጥቃት አንድ ሰው መገደሉ እና ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል። ይህን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በየመን ሆዴይዳ ወደብ አቅራቢያ በሚገኝ ወታደራዊ ኢላማ ላይ በወሰደችው የበቀል እርምጃ ስድሰት ስዎች ሰዎች ሲገደሉ፣ 80 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ደግሞ ሀውቲዎች በሚሳይል ማዕከላዊው እስራኤልን መድረስ ችለዋል። እስራኤል ይህ ሚሳይል ተመትቶ መውደቁን ገልጻለች።
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከሀማስ በተጨማሪ እስራኤል ከየመኑ የሀውቲ ታጣቂ እና ከሊባኖሱ ሄዝቦሃ ጋር እየተዋጋች ነው።
በጋዛ አንድ አመት ባስቆጠረው ጦርነት በርካታ የሀማስ መሪዎችን የገደለችው እና መጠነሰፊ ወድመት ያደረሰችው እስራኤል፣ አሁን ትኩረቷን ወደ ሰሜን በማዞር በሄዝቦላ ይዞታዎች ላይ ድብደባ እያካሄደች ነው።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ባለስልጣናት ተኩስ እንዲቆም ጫና ቢያደርጉም፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሄዝቦላ ላይ "በሙሉ አቅም" ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተዋል።
የእስራኤል "ፖሊሲ ግልጽ ነው"ብለዋል ኔታንያሁ።
"ሄዝቦላን በሙሉ አቅማችን ማጥቃታችንን እንቀጥላለን፤ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው መመለስን ጨምሮ ሁሉንም ግቦቻችንን ሳናሳካ አናቆምም" ብለዋል።
የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላ ቦሀቢብ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ "በሁሉም ግንባሮች" አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ ይህ የቀጠለው ግጭት ካልቆመ፣ ቀጣናዊ እና አለምአቀፋዊ ሰላም እና መረጋጋትን አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል ቅርቃር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።