
የሶሪያ አማጽያን የሀገሪቱ ዋና ከተማ ደማስቆን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል
ለ24 ዓመታት የዘለቀው የበሽር አል አሳድ አገዛዝ ማብቃቱን የሶሪያ ጦር አዛዥ ለሀገሪቱ ጦር አመራሮች ማሳወቃቸው ተነግሯል።
የበሽር አል አሳድ አገዛዝ ያበቃው ከሰሞኑ ዓለምን ያስገረመው ፈጣኑ የአማጽያን ግስጋሴን ተከትሎ እንደሆነ የሶሪያ ጦር አዛዥ እንዳሳወቋቸው የሀገሪቱ ጦር አመራረር ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ሶሪያን ለ24 ዓመታት የገዙት ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ትናነት ማለዳ ላይ አውሮፕላን ተሳፍረው ስፍራው ለጊዜው ወዳልታወቀ ቦታ መኮብለላቸው ተነግሮ የነበረ ሲሆን፤ በኋላ ላይ ሞስኮ መግባታቸው የሩሲያ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
በአሁኑ ወቅትም በፍጥነት የሶሪያ ከተሞችን በመቆጣጠር ላይ የነበሩ አማጽያን ወደ ደማስቆ ከተማ መግታቸውም ነው የተገለጸው።
“ደማስቆ ከበሽር አል አሳድ አገዛዝ ነጻ ሆናለች” ያሉ የሶሪያ አማጽየን በቴሌቭዥን መስኮት ቀርበው ለሶሪያ ህዝብ የመጀመሪያን መግለጫ መስጠታቸውን ሁለት የአማጽያን ምንጮች አስታውቀዋል።
ከኢድሊብ የተነሳው ሃያት ታህሪር አል-ሻም አማጺ ቡድን ባለፉት ቀናት በአላሳድ ጦር ላይ በከፈተው ጥቃት፥ አሌፖ፣ ሃማ እና ሆምስ የተሰኙ ቁልፍ ከተሞችን መቆጣጠሩ ይታወሳል።
የአማጺ ቡድኑ ግስጋሴውን በመቀጠልም ነው በዛሬው እለት የሶሪያ ርዕሰ መዲናዋን ደማስቆ ከአላሳድ አገዛዝ ነጻ ማውጣቱን ያስታወቀው።
ይህንን ተከትሎም 53 ለሚያህሉ ዓመታት ዘልቆ የቆየው የአባትና ልጅ የአገዛዝ ዘመን ማብቃቱ ነው የተነገረው።
የፕሬዝዳንት በሽል አል አሳድ አባት የሆኑት ሃፌዝ አል አሳድ ሶሪያን ከፈረንጆቹ 1971 አስከ 2000 ድረስ በፕሬዝዳትነት መርተዋል።
ልጃቸው በሽር አላሳድ ደግሞ ከ2000 ጀምሮ ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ዘልቀዋል።