ኢራን ላጋየችው የዩክሬን አውሮፕላን ሰለባዎች በነፍስ ወከፍ 150 ሺ ዶላር መመደቧን አስታወቀች
ከአንድ ዓመት በፊት ኢራን በሚሳይል መትታ ባጋየችው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ 176 ሰዎች ተገድለዋል
ክፍያው እንዲፈጸም የኢራን ካቢኔ ማጽደቁ ተገልጿል
ኢራን ከዓመት በፊት ከቴህራን ተነስቶ ወደ ዩክሬን ኬቭ በመብረር ላይ የነበረውን የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ከተነሳ ብዙም ሳይጓዝ በሚሳይል መትታ መጣሏ ይታወሳል፡፡
እ.ኤ.አ. ጥር 8/2020 በኢራን የአየር ክልል በጋየው በዚህ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ 176 ሰዎች በሙሉ አልቀዋል፡፡ ለነዚህ ሟቾች ፣በእያንዳንዳቸው ስም 150,000 ዶላር ለቤተሰቦቻቸው ለመስጠት መዘጋጀቷን ኢራን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጋለች፡፡ የሀገሪቱን ዜና ወኪል ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ክፍያውን የሀገሪቱ ካቢኔ አጽድቋል፡፡
ኢራን 176 ሰዎች የሞቱበትን የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላንም በሚሳይል ያጋየችው በኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ካምፕ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ሲሆን ይህ እምጃ በስህተት መከናወኑን ሀገሪቱ በወቅቱ አስታውቃለች፡፡
አሜሪከ ዝነኛውን ጄኔራልዋን ቃሲም ሱሌይማኒን መግደሏን ተከትሎ ኢራን በወሰደችው አጸፋዊ እርምጃ ፣ በኢራቅ የሚገኘውን የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ በባለስቲክ ሚሳይል መደብደቧ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሀገራቱ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ፣ አሜሪካን በመጠባበቅ ላይ እንዳለች ነበር በጥርጣሬ የመንገደኞችን አውሮፕላን መምታቷን ያስታወቀችው፡፡
በአውሮፕላኑ ጥቃት ከሞቱት መካከል አብዛኛው ካናዳውያን ናቸው፡፡