የተባበሩት መንግስታት በኢራን ላይ እንደገና ማዕቀብ እንዲጥል አሜሪካ ጠየቀች
የአውሮፓ ሀገራት የ2015ቱ የኑክሌር ስምምነት እንዲከበር እንሰራለን ብለዋል
የአሜሪካ ማስፈራሪያ እና እርምጃ እንደማያሰጋት ኢራን አስታውቃለች
የተባበሩት መንግስታት በኢራን ላይ እንደገና ማዕቀብ እንዲጥል አሜሪካ ጠየቀች
በቴህራን እና በዓለም ኃያላን መካከል በተደረገው የኑክሌር ስምምነት መሰረት በሀገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከተነሳ ከአምስት ዓመት በኋላ የተባበሩት መንግስታት በኢራን ላይ እንደገና የማዕቀብ እጁን እንዲያሳርፍ የአሜሪካ አስፈፃሚ አካል ጠይቋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ እንዳሉት ማዕቀቡ በድጋሚ እንዲጣል የተፈለገው ኢራን እ.ኤ.አ. በ 2015 በተደረሰው ስምምነት “የተጣለባትን ኃላፊነት መወጣት ባለመቻሏ ነው”፡፡
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ድርጅቱ በኢራን ላይ የጣለውን ለ 13 ዓመታት የቆየ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ማራዘም አለመቻሉን የገለጹት ፖምፒዮ ያኔ የተጣለው ማዕቀብ በጥቅምት ወር አጋማሽ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
ማዕቀቡን አለማራዘም ኢራን ከጥቅምት 18 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ሁሉንም ዓይነት የጦር መሣሪያዎች የመግዛት ዕድል እንደሚሰጣት በማንሳት አሜሪካ ማዕቀቡ እንዲራዘም ፊርማዋን ማኖሯንም ፖምፒዮ ተናግረዋል፡፡
ማዕቀቡ ወዲያውኑ ተግባራዊ እንደሚሆንም ነው ሚስተር ፖምፒዮ የገለጹት፡፡
አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ማዕቀቦችን ለማጠናከር እና ደንቦችን የሚጥሱ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የምትወስደቸውን ተጨማሪ እርምጃዎች ይፋ እንደምታደርግም አስታውቀዋል ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ስምምነቱ ለቴህራን ያጋደለ ስጦታ ነው” በማለት ከኢራን ጋር ከተደረሰውን የኑክሌር ስምምነት አሜሪካን በ 2018 አግልለዋል፡፡
የአውሮፓ ሀገራት በአንጻሩ የ2015ቱ የኑክሌር ስምምነት እንዲጠበቅ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ ትናንት ቅዳሜ መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት አስተያየት “የዓለም ኃያላን የአሜሪካን ማዕቀብ መቃወም አሊያም እራሳቸው ማዕቀብ እንደሚገጥማቸው መጠበቅ አለባቸው” ብለዋል፡፡
አሜሪካኖች እንደ ጉልበተኛ ሆነው ማዕቀቦችን ባሻቸው ሰዓት በፈለጉት ሀገር ላይ እንደሚጥሉ የተናገሩት ሚኒስትሩ ጃቫድ ዛሪፍ ሌሎች ሀገራት ይህን የአሜሪካ ውሳኔ ካልተቃወሙ ነገ እነርሱም ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊያውቁ ይገባል ብለዋል፡፡
“በአሜሪካ ማስፈራሪያ አንሰጋም ፤ ስራችንን እንቀጥላለን ፤ መብታችን ከተነካ የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉም ተናግረዋል ዘ ናሺናል እንደዘገበው፡፡