ግለሰቡ ውሻ የሚያስመስሉትን ነገሮች ሲያደርግ ታይቷል
ጃፓናዊው ግለሰብ ለብዙዎች እንግዳ ቢሆንም የልጅነት ምኞቴን አሳክቼዋለሁ ብሏል።
15 ሺህ ዶላር ወጪ ያደረገበት የአመታት ህልሙም በቶኪዮ ጎዳናዎች ላይ ተገልጧል።
ቶኮ የተባለው ግለሰብ ሁለት እጆቹን እግር አድርጎ፤ ሰውነቱን በሙሉ ውሻ በሚያስመስሉ አልባሳት ሸፍኖ ሲንቀሳቀስ የተመለከቱት ሰዎች በፍጹም የሰው ልጅ ይሆናል ብለው አልጠረጠሩም።
“ውሻ” የመሰለው ቶኮ መሬት ላይ በመንከባለልና ሌሎች ውሻዎች የሚያደርጓቸውን ነገሮች ሲፈጽምም ሰዎች ሰብሰብ እያሉ ተመልክተውታል።
ከ30 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው በግለሰቡ ዩቲዩብ ገጽ ላይ ከተለጠፈው ምስል ስር ቶኮ “የልጅነት ህልሜን አሳክቻለሁ” የሚል ጽሁፍ አስፍሯል።
“የልጅነታችን ምኞታችሁን ታስታውሳላችሁ? ጀግና የመሆን ወይም የተለየ ነገር ማድረግ እንፈልጋለን፤ እኔ ውሻ የመሆንና እንደ ውሻ የመጓዝ ምኞት ነበረኝ፤ ይህንንም በምርቃት መጽሃፋችን ውስጥ አስፍሬው ነበር” ይላል።
ቶኮ ከዴይሊሜል ጋር ባደረገው ቆይታ “ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ መሆን የምፈልገውን (ውሻ መሆን) ስነግራቸው ስለሚያፌዙብኝ መናገሩን አቁሜያለሁ” ሲል ተናግሯል።
ከስራ ባልደረቦቹ ሊደርስበት የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቀነስም ሙሉ ስሙን አይናገርም፤ በዩቲዩብ ገጹም ፎቶውን የሚያሳይ አንዳች ነገር አላጋራም።
ቶኮ የልጅነት ህልሙን ለማሳካት ውሻ የሚያስመስለውን ልብስ ለፊልም ስራዎች የሚውሉ አልባሳትን በመስራት ከሚታወቀው “ዜፔት” የተሰኘ ኩባንያ በ15 ሺህ ዶላር አሰርቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ልብስ ለብሶ በግቢያቸው ውስጥ እንደ ውሻ ሲንቀሳቀስ የተሰማውን እንግዳ የመረበሽ ስሜትን ያልደበቀው ቶኮ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ እንሰሳ የመሆን የልጅነት ፍላጎቱ አሁንም እንዳልቀነሰ ግን ይናገራል።