ቢሊየነሩ መስክ እና በተመድ የኢራን አምባሳደር ሚስጢራዊ ውይይት ማድረጋቸው ተሰማ
የዋሽንግተን እና ቴህራንን ግንኙነት ለማሻሻል ያለመው ውይይት በኒውዮርክ መካሄዱ ተገልጿል
መስክ የመንግስት አሰራርን ለማቀላጠፍ የሚቋቋመውን አዲስ ቢሮ እንዲመሩ በትራምፕ መሾማቸው ይታወሳል
የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኤለን መስክ እና በመንግስታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር አሚር ሳይድ ኢራቫኒ ሚስጢራዊ ውይይት ማድረጋቸው ተነገረ።
ኒውዮርክ ታይምስ የኢራን ባለስልጣናት ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው በኒውዮርክ የተካሄደው ምክክር ከአንድ ስአት በላይ የቆየ ነበር።
ምክክሩ የአሜሪካ እና ኢራንን የሻከረ ግንኙነት ለማስተካከል ያለመ እንደነበርም ነው ዘገባው የጠቀሰው።
ሲኤንኤን በበኩሉ በውይይቱ ዙሪያ የትራምፕ የሽግግር ጊዜ ቡድንን፣ ኤለን መስክን እና በመንግስታቱ ድርጅት የኢራን ተልዕኮን አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቆ ምላሽ እንዳላገኘ ዘግቧል።
በተመድ የባይደን አስተዳደር አመራሮችም በሚስጢራዊው ውይይት ዙሪያ ምንም መረጃ እንደሌላቸውም ነው የጠቆመው።
የትራምፕ ዳግም መመረጥ በኢራን ላይ “ከባድ ግፊት” ይፈጥራል ተብሎ በተሰጋበት ወቅት ተደረገ የተባለው ምክክር በመሪዎች ደረጃ ከተካሄደ ውጥረቱን ሊያረግበው ይችላል።
የሪፐብሊካኑን ተመራጭ ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን የሚያወሱ ተንታኞች ግን ትራምፕ በኢራን ላይ አዲስ ፖሊሲ የሚከተሉ አይመስልም ይላሉ።
አሜሪካን ከ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት በ2018 ያስወጡት ትራምፕ ቴህራን በስምምነቱ ተነስተውላት የነበሩ ማዕቀቦች ዳግም እንዲተገበሩ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢራንም የዩራኒየም ማበልጸግ ሂደቷን ከማፋጠን ባሻገር የነዳጅ የወጪ ንግዷን በእጅጉ ጨምራለች።
በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች የምታደርገውን ድጋፍ ማጠናከሯም ለአሜሪካ ዋነኛ አጋር እስራኤል ከፍተኛ ስጋት ደቅኖ እርስ በርስ ሃይላቸውን እስከመለካካት ደርሰዋል።
በቅርቡ የመንግስትን አሰራር ለማቀላጠፍ ይቋቋማል የተባለውን አዲስ ተቋም እንዲመሩ የተሾሙት መስክ ከኢራን ባለስልጣን ጋር መምከራቸው የትራምፕ አስተዳደር በቀጣዮቹ አራት አመታት በቴህራን ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ይቀየራል ወይ የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
ትራምፕ ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በኋላ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ለማስተላለፍ ሲደውሉላቸው ከመስክ ጋር በቀጥታ ማገናኘታቸው ይታወሳል።
የቴስላ እና ስፔስኤክስ ስራ አስፈጻሚው ኤለን መስክ አዲሱ ሹመታቸው ከግል የንግድ ፍላጎታቸው ጋር ሊጋጭ ይችላል የሚል ስጋት ከወዲሁ አጭሯል።