እስራኤል ሊባኖስን ስትደበድብ፤ ሄዝቦላህም የአጸፋ ምት በእስራኤል ላይ ፈጽሟል
እስራኤል በቤሩት በፈጸመችው ከባድ ድብደባ ቢያንስ 20 ሰዎች ተገድለዋል
ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ በወሰደው የአጸፋ ምት የሰዎች ህይወት አልፏል ተብሏል
እስራኤል አዳሩን እንዲሁም ዛሬ ማለዳ ላይ በሊባኖስ ከባድ የተባለ ድብደባ የፈጸመች ሲሆን፤ ሄዝቦላህም የእስራኤል ላይ የአጸፋ ምት መፈጸሙ ተነግሯል።
የእስራኤል የጦር ጄቶች በቤሩት ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ እና የሄዝቦላህ ይዞታ በሆኑ ስፍራዎች ላይ ከትናንት ቀን ጀምሮ ከባድ ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፤ በዚህም ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ነው የተባለው።
የእስራኤል ጦር ለሲቪል ነዋሪዎች በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የማስጠንቀቂያ መልእክት ካሰራጨ በኋላ በቤሩት ዳሂየ አካባቢ በፈጸመው ድብደባ የሄዝቦላህ መሳሪያዎች እና ሚሳዔሎችን ማውደሙ ተነግሯል።
የሊባኖሱ ቡድን ሄዝቦላህም ለእስራኤል ጥቃት የአጸፋ መልስ ምት መስጠቱ ተነግሯል።
በዚህም በሰሜን እስራኤል ናሃሪያ ከተማ በመኖሪያ ቤት ህንጻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የእስራኤል ፖሊስ አስታውቋል።
ሄዝቦላህ በናሃሪያ ከተማ ለተፈጸመው የድሮን ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ ሲሆን፤ የድሮን ጥቃቱ ዋነኛ ኢላማ በናሀሪያ ከተማ ምስራቅ ላይ የሚገኝ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እንደሆነም ገልጿል።
በሰሜናዊ እስራኤል የተለያዩ ክፍሎችም የድሮን እና የሮኬት ጥቃቶች መፈጸማቸውን ያስታወቀው የእስራኤል ጦር፤ በርካታ እስራኤላውያን ከጥቃቱ መሸሸጋቸውን እና የተጎዳ ሰው አለመኖሩንም አስታውቋል።
እስራኤል እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ወደ ግጭት ያመሩት የእስራኤል ጋዛ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን፤ ካሳለፍነው መስከረም ወር ወዲህ ደግሞ ወደ ለየለት ጦርነት ገብተዋል።
እስራኤል ሀሰን ነስረላህን ጨምሮ ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራሮችን የገደለች ሲሆን፤ ቤሩትን ጨምሮ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ በርካታ ከተሞችን በአየር ድብደባ አውድማለች።
በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተገደሉ ሊባኖሳውያን ቁጥር 3 ሺህ 287 የደረሰ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ እዛኞቹ ባለፉት ሰባት ሳመንታት ውስጥ የተገደሉ መሆኑን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል እና በእስራኤል ይዞታ ስር በሚገኙ የጎላን ተራች ላይ በፈጸመው ጥቃት ከ100 በላይ እስራኤላውያን መሞታቸው ተነግሯል።